ሩሲያ ፕሬዝደንት ዘለንስኪን በወንጀል ከምትፈልጋቸው ሰዎች ዝርዝር ውስጥ አካተተች
ዩክሬን ይህ የሞስኮን ተስፋ መቁረጥ የሚያሳይ ነው ስትል አጣጥላዋለች
ሩሲያ በዩክሬን ልዩ ያለችው ዘመቻ ከጀመረች ከየካቲት 2022 ወዲህ በበርካታ የዩክሬን እና የአውሮፓ ፖለቲከኞች ላይ የእስር ማዘዣ አውጥታለች
ሩሲያ ፕሬዝደንት ዘለንስኪን በወንጀል ከምትፈልጋቸው ሰዎች ዝርዝር ውስጥ አካተተች።
ሩሲያ በዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ላይ የወንጀል ክስ መመስረቷን እና ከምትፈልጋቸው ግለሰቦች ዝርዝር ውስጥ ማካተቷን ሮይተርስ የሩሲያውን የዜና አገልግሎት ታስን ጠቅሶ ዘግቧል።
ዩክሬን ይህ የሞስኮን ተስፋ መቁረጥ የሚያሳይ ነው ስትል አጣጥላዋለች።
ታስ እንደዘገበው ከሆነ የሩሲያ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር መዝገብ ዘለንስኪን በተፈላጊዎች ዝርዝር ውስጥ አካቷቸዋል።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በአለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ማዘዣ እንደወጣባቸው አስታውሷል።
የሩሲያን እርምጃ ዋጋ የሌለው መሆኑን የገለጸው ሚኒስቴሩ "አለምአቀፉ ፍርድቤት የሩሲያው አምባገነን በጦር ወንጀል ተጠርጥረው በ123 ሀገራት ተፈጻሚ የሚሆን የእስር መያዧ እንዳወጣባቸው ልናስታውሳቸው እንወዳለን" ብሏል።
"ይህ የሩሲያ እርምጃ በሌላ መንገድ ትኩረት መሳብ ያልቻለው የሩሲያ መንግስትና ፕሮፓጋንዳ ተስፋ መቁረጡን የሚያሳይ ምልክት ነው" ብሏል ሚኒስቴሩ።
ሩሲያ በዩክሬን ልዩ ያለችው ዘመቻ ከጀመረች ከየካቲት 2022 ወዲህ በበርካታ የዩክሬን እና የአውሮፓ ፖለቲከኞች ላይ የእስር ማዘዣ አውጥታለች።
ሩሲያ ባለፈው አመት በፑቲን ላይ የእስር ማዘዣ ባወጡት የአለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አቃቤ ህግ ላይ የእሰር መያዣ አውጥታለች።