ሶማሊያን ክፉኛ ያስቆጣው የሶማሊላንድና የኬንያ ወዳጅነት የቀጣናው ሌላ ፈተና ሆኗል
የኬንያ መንግስት በሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሀርጌሳ ቆንስላ ጽ/ቤት ሊከፍት መሆኑን አስታወቀ፡፡ የሀገሪቱ መንግስት ይህን ያለው የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በኬንያ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ መሆኑን ብሉምበርግ ጽፏል፡፡ የኬንያ ቆንስላ ጽ/ቤት በሀርጌሳ ይከፈታል የተባለው እ.ኤ.አ. በመጪው መጋቢት 2021 ነው፡፡
ሶማሊላንድም በናይሮቢ ያላትን ጉዳይ ማስፈጸሚያ ቢሮ ወደ ቆንስላ ጽ/ቤት ለማሳደግ ማቀዷን አስታውቃለች፡፡ እንደ ብሉምበርግ ዘገባ የኬንያ አየር መንገድን ጨምሮ ሌሎች አየር መንገዶች ከናይሮቢ ወደ ሀርጌሳ ከመጋቢት ወር ጀምሮ በረራ እንዲያደርጉ የሚያስችል ውይይት በናይሮቢ ተደርጓል፡፡ ናይሮቢና ሀርጌሳ በእርሻ እና ሽብርተኞችን በጋራ መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች እንዲሁም በሌሎችም የሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያተዋልም ተብሏል፡፡
የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከሶማሊላንዱ መሪ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ተከትሎ ሞቃዲሾ ከናይሮቢ ጋር ያላትን ግንኙነት ማቋረጧ ይታወሳል፡፡ ሶማሊያ በኬንያ የሚገኙ ዲፕሎማቶቿ ከነቤተሰቦቻቸው ሀገሪቱን ለቀው እንዲመለሱም አዛለች፡፡
ሶማሊላንድ እ.ኤ.አ. በ 1991 በሀገሪቱ ከነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት በኋላ ራሷን የቻለች ሀገር መሆኗን ያወጀች ሲሆን እስካሁን ግን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዕውቅና አልተሰጣትም፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዕውቅና እንዲሰጣት ሌት ከቀን የምትታትረው ሶማሊላንድ እስካሁን ከየትኛውም ዓለም አቀፍ ተቋምም ሆነ ሀገር ሉዓላዊ ሀገር መሆኗን የሚገልጽ ዕውቅና ማግኘት አልቻለችም፡፡