ፕሬዝዳንት ፋርማጆ “ቀጣዩን ምርጫ ለማጭበርበር እየሰሩ ነው” የሚል ተቃውሞ ገጥሟቸዋል
የሶማሊያውን ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ (ፋርማጆን) የሚቃወም ሰልፍ በሞቃዲሾ ከተማ መካሄዱን ጉብጁብ የተሰኘው የሶማሊያ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል፡፡
ዛሬ በተካሄደው የታቃውሞ ሰልፍ ላይ በመዲናዋ ያቅሽድ በሚባለው ስፍራ ላይ ሰልፈኞቹ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው አራት ሰዎች መሞታቸው ተሰምቷል፡፡ እስካሁን ብዙዎች መጎዳታቸው የተዘገበ ሲሆን ተጨማሪ የጸጥታ ኃይሎች በከተማዋ እንዲሰማሩ መንግስት ትዕዛዝ አስተላልፏል ተብሏል፡፡
የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ወደ ከተማዋ ማዕከላት ለመግባት እየተጓዙ ሲሆን የጸጥታ ኃይሎች መንገዶቹን እየዘጉባቸው እንደሆነ ነው በዘገባው የተጠቆመው፡፡ ሰልፈኞቹ የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝ ፋርማጆን በመቃወም ድምጻቸውን አሰምተዋል፡፡
እነዚሁ ሰልፈኞች የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ፣ የጸጥታ ኃላፊዎችንና የመንግስት ሰራተኞችን በጊዜያዊው የፌዴራል ምርጫ ኮሚቴ ውስጥ በማሰማራት ፣ ምርጫውን ለማጭበርበር እየሰሩ ነው የሚል ተቃውሞ እያቀረቡ እንደሆነ ዘገባው አንስቷል፡፡
በተቃዋሚ ፓርቲዎች ድጋፍ እንዳለው የተገለጸው ይህ ሰልፍ ዛሬ ጠዋት ላይ መጀመሩንም ነው የሶማሊ መገናኛ ብዙኃን የዘገቡት፡፡
ሶማሊያ እ.አ.አ በተያዘው የታህሳስ ወር 2020 የምክር ቤት ምርጫ ለማካሔድ ያቀደች ሲሆን ከሁለት ወራት በኋላ በየካቲት 2021 ደግሞ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለማድረግ መዘጋጀቷን አስታውቃለች፡፡