አረብ ኤምሬትስ በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ "ዓለም አቀፋዊ መግባባትን ለማምጣት የፈጠራ ስርዓት እያዘጋጀሁ ነው" አለች
የአረብ ኤምሬትስ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ከፈረንጆቹ ህዳር 30 እስከ ታህሳስ 12 በዱባይ ታስተናግዳለች
በጉባኤው ጥራት ያለው አጋርነት፣ ውጤትና መፍትሄዎች ላይ ለመድረስ ስራዎች ይሰራሉ ተብሏል
አረብ ኤምሬትስ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን በምታስተናግድበት ወቅት ዓለም አቀፍ መግባባትን ለማምጣት ፈጠራ ያለው የባለብዙ ወገን ስርዓት ለማስተዳደር እየሰራች መሆኗን አስታውቃለች።
ኤምሬትስ መጭው ህዳር የሚካሄደው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ 28) አዘጋጅ ሀገር ናት።
የውጭ ጉዳይና የዓለም አቀፍ ትብብር ሚንስትርና የጉባኤው አዘጋጅ ብሄራዊ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን ዓለም አቀፍ መግባባትን ለመፍጠር በፈጠራ የተደገፈ ስርዓት ለማስተዋወቅ ቁርጠኛ ነን ብለዋል።
በጉባኤው ጥራት ያለው አጋርነት፣ ውጤትና መፍትሄዎች ላይ ለመድረስ ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል።
በሰባተኛው የአዘጋጅ ኮሚቴው ስብሰባ ላይ ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን የአየር ንብረት ለውጥ የዚህ ወቅት "ዋና ፈተና" መሆኑን ገልጸዋል።
በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በፈረንጆቹ ከህዳር 30 እስከ ታህሳስ 12 በዱባይ ስለሚካሄደው የጉባኤ ዝግጅት ውይይት ተካሂዷል።
ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናህያን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ካላት አስቸጋሪ የአየር ንብረት ሁኔታ አንጻር የአየር ንብረት ለውጥና የሚያስከትለውን መዘዝ ለመከላከል ትልቅ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን እንረዳለን ብለዋል።
በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሙቀት መጠን የመጠበቅ ግብ ላይ ለመድረስ አስፈላጊነቱን እንገነዘባለን ሲሉ ገልጸዋል።
በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በድርቅ፣ ሙቀት፣ ጎርፍ፣ አውሎ ንፋስ እና ሌሎች አደጋዎች የተጎዱትን ማህበረሰቦች መደገፍ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
"አላማችን የኮፕ 28 ጉባኤ መሻሻልና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጫና የሚገድብ ስኬታማ ውይይት እንዲሆን ነው" ብለዋል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለጉባኤው ያቀረበቻቸው አጀንዳዎች በፍላጎት፣ በተግባር እና ተጠያቂነት ላይ ያተኮሩ እንዲሁም ቃል ከመግባት ባለፈ መሬት የረገጡ እርምጃዎች መሻገር ላይ እንደሚያተኩሩ ተገልጿል።