በሞዛምቢክ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ 40 ቀናት እጾማለሁ ያለው ፓስተር ህይወቱ አለፈ
ፍራንሲስኮ ባራጃህ የተባለው ፓስተር ፥ ለ25 ቀናት ከጾመ በኋላ ሰውነቱ አልቆ ሆስፒታል ውስጥ ህይወቱ ማለፉ ተነግሯል
በደቡብ አፍሪካም ከሰባት አመት በፊት 40 ቀንና ሌሊት ለመጾም ጫካ የገባው ፓስተር ሞቶ መገኘቱ ይታወሳል
በሞዛምቢክ እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ 40 ቀናት እጾማለሁ ያለው ፓስተር ህይወቱ ማለፉ ተገልጿል።
ፍራንሲስኮ ባራጃህ የተባለው ፓስተር ከባዱን ነገር ተጋፍጦ ምዕመኑን ለማስደመም ያደረገው ጥረት ሳይሳካለት በዛሬው እለት ህይወቱ ማለፉ ተረጋግጧል።
ማኒካ በተባለችው ግዛት ነዋሪ የሆነው ፍራንሲስኮ፥ ለ25 ቀናት ከጾመ በኋላ ከሰውነት ተራ ወጥቶ ህይወቱ ማለፉን ቢቢሲ ዘግቧል።
ፓስተሩ ቀናት እየገፉ ሲሄዱ መራመድም ሆነ መቆም ተስኖት እንደነበር የተናገሩት ቤተሰቦቹ፥ ቤይራ በተሰኘችው ከተማ ወደሚገኝ ሆስፒታል ወስደውት ህክምና ሲደረግለት ቆይቷል።
የህክምና ክትትሉ ግን የፍራንሲስኮ ባራጃህ “በድንቅ መዝገብ ስሙን የማስፈር ሙከራ” ሊያሳካው አልቻለም።
ቤተሰቦቹም ሆነ የሚያገለግለው ቤተእምነት ምዕመናን እንደማይተርፍ የገባቸው አስቀድሞ መሆኑን የጠቀሰው የቢቢሲ ዘገባ፥ በህልፈቱ ብዙም አለመደናገጣቸውን አመላክቷል።
በደቡብ አፍሪካም ተመሳሳይ ሙከራ የ44 አመቱን ፓስተር ህይወት መቀማቱ የሚታወስ ነው።
አልፈርድ ንድሎቩ የተባለው ፓስተር ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ቆይታው የጾመውን 40 መአልትና ሌሊት ጾም ሪከርድ እሰብራለሁ ብሎ ቢዝትም ቀድሞ ተሰብሯል።
አልፈርድ ከሰዎች ርቆ ጫካ ውስጥ ጾምና ጸሎት መጀመሩን የሚጠቅሰው የዚምባቡዌው ኒውስዴይ ጋዜጣ፥ ከቤቱ ከወጣ ከ30 ቀናት በኋላ አስከሬኑ መገኘቱን አውስቷል።
ጫካ ውስጥ የሞተ ሰው ተመልክቻለሁ ያለ አዳኝ ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠቱና በተደረገው ምርመራ የሟች አስከሬን ለቤተሰቦቹ ተሰጥቶ መቀበሩንም ነው ዘገባው ያስታወሰው።
ጓደኞቹም ሆነ ቤተሰቦቹ ጠንካራና ጤናማ አገልጋይ የነበረው አልፈርድ ለሞት እጁን ይሰጣል ብለው ያለመገመታቸውና ራሱን በጫካ ውስጥ መደበቁ ለህክምና እንኳን ሳይበቃ እንዲሞት አድርጎታል።
አልፈርድ ለምን ያህል ቀን ጾሞ ህይወቱ እንዳለፈም ማወቅ ሳይቻል ይህቺን አለም ተሰናብቷል።
በአፍሪካ እንደ እነ ፍራንሲስኮ እና አልፈርድ ሁሉ የማይቻሉ የሚመስሉ ተአምራትን ለመፈጸምና ቀልብን ለመሳብ ጥረት የሚያደርጉ ፓስተሮች እየተበራከቱ መምጣታቸው ይነገራል።