ኬንያዊያን በሐቀኝነታቸው የሚወዷቸው ሪጋቲ ጋቻጉ ከምክትል ፕሬዝዳንትነት ሊነሱ ነው
ጋቻጉ አባታቸው ማው ማው በሚል የሚታወቀው የጸረ ቅኝ ግዛት ዘመቻ መሪነታቸው ይታወቃሉ
የፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ምክትል የሆኑት ጋቻጉ የህዝብ ተቃውሞ እንዲባባስ ድጋፍ አድርገዋል በሚል ከስልጣናቸው ሊነሱ ይችላሉ ተብሏል
ኬንያዊያን በሐቀኝነታቸው የሚወዷቸው ሪጋቲ ጋቻጉ ከምክትል ፕሬዝዳንትነት ሊነሱ ነው፡፡
ሪጋቲ ጋቻጉ ከፈረንጆቹ 2017 ጀምሮ የኬንያ ህግ አውጪ ምክር ቤት አባል ሆነው መረጥ ችለዋል፡፡
ቀስ በቀስም የኬንያ ዋነኛ ፖለቲከኛ መሆን የቻሉት እኝህ ሰው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ባዋቀሩት መንግስት ውስጥ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነዋል፡፡
ይሁንና አሁን ላይ እኝህ ጉምቱ ፖለቲከኛ በኬንያ በተካሄደው አመጽ እጃቸው አለበት በሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን ከስልጣን እንዲነሱ እንቅስቀሴ እየተካሄደባቸው መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
አባታቸው በብሪታንያ የጸረ ቅኝ ግዛት ወቅት ማው ማው ንቅናቄን በማደራጀት እና ባደረጓቸው ሌሎች ጥረቶች በኬንያዊያን ተወዳጅ ሲሆኑ እሳቸው ደግሞ የኬንያዊያንን እውነተኛ ችግሮች በመናገራቸው ይወዳደሉ፡፡
በቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሮ ኬንያታ ጊዜ ጀምሮ ቁልፍ የሀገሪቱ ፖለቲከኛ የሆኑት ጋቻጉ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ካቢኔ አባልም ናቸው፡፡
እሳቸው አባል የሆኑበት የፕሬዝዳንት ሩቶ አስተዳድር ተጨማሪ ገቢ በግብር መልክ ለማግኘት ያረቀቀው ፖሊሲ በህዝባዊ አመጽ መቀልበሱ ይታወሳል፡፡
ጀርመን 250 ሺህ ስራ ፈላጊ ኬንያውያንን ለመቀበል ስምምነት ፈጸመች
ከዚህ ህዝባዊ ተቃውሞ ጀርባ ጋቻጉ እጃቸው አለበት በሚል ወቀሳ የቀረበባቸው ሲሆን ከፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ጋርም ግጭት ውስጥ እንደገቡ ተገልጿል፡፡
ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በምርጫው እንዲያሸንፉ ጋቻጉ በተለይም የታችኛው ማህበረሰብ ድምጹን ለሩቶ እንዲሰጥ የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር፡፡
ይህን ተከትሎ የኬንያ ህግ አውጪ ምክር ቤት ጋቻጉ ከምክትል ፕሬዝዳንትነታቸው እንዲነሱ ድምጽ ለመስጠት በሂደት ላይ ነው ተብሏል፡፡
እስካሁን በተደረገ የቅድመ ድምጽ ውጤት መሰረት አብዛኛው የሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ጋቻጉ ከስልጣን እንዲነሱ ድምጽ እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ፕሬዝዳንት ጋቻጉ በበኩላቸው የቀረበባቸውን ክስ እንዳልፈጸሙ ተናግረው የህዝብ ድምጽን ማስተጋባቴን እቀጥላለሁ ብለዋል፡፡