አዲሱ የመውጫ መንገድ በአምስት ወራት ውስጥ በቻይና እና ኬንያዊያን ተቋራጮች ተገንብቷል
ኬንያ በአጼ ሀይለስላሴ ስም የሰየመችውን ፈጣን መንገድ አስመረቀች።
ጎረቤት ሀገር ኬንያ የፈጣን መንገዷን መውጫ ኢትዮጵያን ከ40 ዓመት በላይ ለመሩት እና የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በመሰረቱት አጼ ሀይለስላሴ ስም ሰይማለች።
ካሳለፍነው ሀምሌ ጀምሮ የተገነባው ይህ የፈጣን መንገድ መውጫ በናይሮቢ ዋና የትራፊክ ፍሰትን ለማቀላጠፍ በሚል በቻይና እና የኬንያ ተቋራጮች ተገንብቷል።
መንገዱ ከዛሬ ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉ በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ሁለት ሰዓት ይፈጅ የነበረውን መንገድ ወደ 20 ደቂቃ ዝቅ እንዲል እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ባለ አምስት መስመር ያለው ይህ የመውጫ መንገድ ከናይሮቢ በፍጥነት ለመውጣት እንደሚያስችል የኬንያ ትራንስፖርት ሚንስትር ኪፕቾምባ ሙርኮመን ተናግረዋል።
ሚንስትሩ አክለውም አዲሱ መንገድ ወደ ማዕከላዊ የቢዝነስ ቦታዎች እና መንግስታዊ ተቋማት አካባቢ ያሉ መጨናነቆችን ያስቀራልም ብለዋል።
የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በክፍያ ይጠቀማሉ የተባለ ሲሆን በቀን 65 ሺህ አሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም እንዳለውም ተገልጿል።