ኬንያ ለፈጥኖ ደራሽ መሪ ጄነራል መሃመድ ሀምዳን ዳጋሎ ያደረገችው አቀባበል ሱዳንን አሰቆጥቷል
የሱዳን መንግስት በኬንያ የሚገኙትን የሀገሪቱን አምበሳደር ለምክክር መጥራቱን አስታወቀ።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ በናይሮቢ የሱዳን አምባሳደር ወደ ካርቱም እንዲመለሱ የተጠሩት ለመክክር ነው።
እንዲሁም ሱዳን አምባሳደሯን የጠራችው የኬንያ መንግስት ለሱዳን ፈጠኖ ደራሽ ሃይሎች አዛዥ ሌተናል ጀነራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ ላደረገችው ይፋዊ አቀባበል ተቃውሞ ለመግለጽ ነው።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ “የኬንያ መንግስት በሌተናል ጀነራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ በሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል የተፈጸሙ ዘግናኝ የሰብዓው መብት ጥሰቶችን እንዲሁም በሀገሪቱ እና በዜጎች ላይ ያደረሰውን ጉዳት ዘንግቷል” ብሏል።
ሱዳን ከናይሮቢ አምባሳደሯ ጋር የሚኖራት ምክክር በሱዳን እና በኬንያ ግንኙነት የወደፊት እጣ ፈንታን የሚወስን እንደሆነም የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አስታውቋል።
ጄነራል ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) ዘጠኝ ወራት ካስቆጠረው ጦርነት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በኡጋንዳ፣ ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ እንዲሁም ባሳለፍነው ረቡዕ በኬንያ ጉብኝት አድርገዋል።
ይህንን ተከትሎም የሱዳን ጦር መሪው አብዱልፈታህ አልቡርሃን ተፋላሚያቸውን ጀነራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ ተቀብለው ያስተናገዷቸውን ሀገራት አጥብቀው መቀወማቸው ይታወሳል።
“የሱዳን ህዝብን እያጠፋ ያለ ቡድንን መሪ ተቀብሎ ማነጋገር ወንጀሉን እንደመተባበር ይቆጠራል” ያሉት የሱዳን ጦር መሪው፥ ሀገራቱን በስም ባይጠቅሱም ዳጋሎን ያስተናገዱት ሀገራት በስልጣን ላይ ላለው መንግስት እውቅና ለመስጠት የሚቸገሩ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
የሀገራቱ ድርጊት ጸብ አጫሪ መሆኑን በመጥቀስም የሱዳንን ሉአላዊነት እና ደህንነት ለማረጋገጥ እርምጃ የመውሰድ መብት አለን ብለዋል።
ጀነራል አልቡርሃን ዳጋሎን ባስተናገዱት ሀገራት ላይ ምን አይነት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ግን አልጠቀሱም።