በኬንያ 95 ተማሪዎችን ሆስፒታል ያስገባ ሚስጢራዊ በሽታ
እስካሁን ምንነቱ በውል ያልታወቀው በሽታ የተማሪዎችን እግር አላንቀሳቅስ ብሏል
በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ያጠቃው በሽታ ትምህርት ቤት እንዲዘጋ አድርጓል
በኬንያ ምንነቱ ያልታወቀ በሽታ መዛመቱን መቀጠሉ አሳሳቢ ሆኗል።
ከመዲናዋ ናይሮቢ 374 ኪሎሜትር ርቆ በሚገኘው የሴቶች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 95 ተማሪዎቹ ታመው ሆስፒታል ገብተዋል።
"ሴንት ቴሬዛ" የተሰኘው ትምህርት ቤት ተማሪዎች የገጠማቸው ህመም እግራቸውን ማንቀሳቀሳ የሚከለክል (ፓራላይዝ) የሚያደርግ ነው።
የኬንያ ትምህርት ሚኒስቴር ከትምህርት ቤቱ አመራሮች ጋር በመምከር ትምህርት ቤቱ እንዲዘጋ ተወስኗል።
በበሽታው በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች መጠቃታቸውን የገለፁት የኬንያ መገናኛ ብዙሃን፥ ስለበሽታው ምንነት ግን እስካሁን በውል የታወቀ ነገር የለም ብለዋል።
የተማሪዎቹ የደም ናሙና ወደ ኬንያ የህክምና ጥናት ተቋም የተላከ ሲሆን በቅርቡም ውጤቱ ይገለፃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።
የበሽታውን ምንነት አውቆ የመፍትሄ አቅጣጫዎች እስኪቀመጡ ድረስም ወላጆች ሳይረበሹ ልጆቻቸውን እንዲከታተሉ የአካባቢው አስተዳደር አሳስቧል።
ትምህርት ቤቱ ሚስጢራዊው በሽታ መላ እስኪፈለግለት ዝግ ሆኖ ይቆያልም ነው የተባለው።