ኬንያዊያን በራይላ ኦዲንጋ አስተባባሪነት የኑሮ ውድነቱን በመቃወም ተከታታይ ሰልፎችን በማድረግ ላይ ናቸው
ኬንያዊው ወጣት በኑሮ ውድነት ምክንያት ራሱን በእሳት አቃጠለ።
በጎረቤት ሀገር ኬንያ ዜጎች በየሳምንቱ ወደ አደባባይ በመውጣት መንግሥት ለኑሮ ውድነት ትኩረት እንዲሰጥ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ላይ ናቸው።
በኬንያ ዋና ዋና ከተሞች እየተካሄደ ባለው በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ የቀድሞው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ላይ ተወዳዳሪ የነበሩት እና በምርጫው የተሸነፉት ራይላ ኢዲንግ እያስተባበሩት ይገኛሉ።
በሀገሪቱ ካሉ የንግድ እና የቱሪዝም ማእከል በሆነችው ሞምባሳ አንድ ወጣት ወደ አደባባይ በመውጣት ራሱን በእሳት አያይዟል።
ወጣቱ የኬንያን ሰንደቅ ዓላማ በመያዝ ራሱን ያቃጠለው የኑሮ ውድነት ፈተና ሆኖብኛል በሚል እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል።
ራሱን በእሳት ያያዘው ይህ ወጣት ሰዎች ባደረጉለት እርዳታ ህይወቱ በቃጠሎው እንዳያልፍ ረድቶታል ተብሏል።
ኬንያዊያን ከኑሮ ውድነት ሰልፍ በተጨማሪ ባሳለፍነው ዓመት የተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተጭበርብሯል በሚልም ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶን እየተቃወሙ ይገኛሉ።
በኬንያ እየጨመረ የመጣውን አለመረጋጋት እና ሰላማዊ ሰልፍ ለማርገብ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና ተቃዋሚያቸው ራይላ ኦዲንጋ ውይይት ለማድረግ ተስማምተዋል።