የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ካቢኔያቸውን በተኑ
"የህዝባችን ድምጽ ሰምተናል" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፥ የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄዎች የሚመልስ አዲስ ካቢኔ አዋቅራለሁ ብለዋል
ኬንያ ለመጨረሻ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ካቢኔዋን የበተነችው በ2005 በፕሬዝዳንት ሙዋይ ኪባኪ የስልጣን ዘመን ነበር
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ሁሉንም ካቢኔዎቻቸውን በተኑ።
ፕሬዝዳንቱ ዛሬ ከሰአት በኋላ ለህዝቡ በይፋ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ 24 ካቢኔዎችን ሙሉ ለሙሉ በመበተን የማሻሻያ እርምጃዎችን ጀምረናል ብለዋል፡፡
ከካቢኔ ጽህፈት ቤት እና ከዲያስፖራ ጉዳዮች ቢሮ ዋና ጸሀፊዎች ውጭ ሁሉንም አመራሮች በቅርቡ እንደሚተኩ ቃል የገቡት ሩቶ የህዝባችንን ድምጽ ሰምተናል ነው ያሉት፡፡
የብድር እዳ ጫና ፣ የኑሮ ውድነት ፣ የስራ አድል ፈጠራ እና ሌሎችም መሰረታዊ ሀገራዊ ችግሮች ላይ መፍትሄ ሊሰጡ የሚችሉ አዳዲስ ካቢኔዎችንም አዋቅራለሁ ብለዋል፡፡
ውሳኔው ተቃውሞውን በማብረድ እና ለህዝቡ ጥያቄ ምን ያህል አስተማማኝ ምላሽ ሊሰጥ እንደሚችል ባይታወቅም ፕሬዝዳንቱ የመጀመሪያው እርምጃ ነው ብለውታል
የኬንያ መንግስት 2024/25 ባቀረበው ረቂቅ የታክስ ህግ፣ የበጀት ጉድለት ለመምሙላት እና ብድር ለመቀነስ ከታክስ በተጨማሪ 2.7 ቢሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ አላማ በማድረግ ህጉን በፓርላማ አጸድቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡
የኬንያ ብድር ከሀገሪቱ አጠቃላይ ገቢ ጋር ሲነጻጸር 68 በመቶ ሲሆን የዓለም ባንክ እና አለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም(አይኤምኤፍ) እንዲሆን ከሚጠብቁት 55 በመቶ ከፍ ያለ ነው።
የሀገሪቱ የፋይናንስ ሚኒስተር መንግስት ያቀደውን ታክስ የማይሰበስብ ከሆነ በ2024/25 የበጀት አመት 1.56 ቢሊዮን ዶላር ክፈጉድለት እንደሚፈጥርበወቅቱ ተናግረው ነበር፡፡
የታክስ ጭማሪው የኑሮ ውድነትን ያንራል፤ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ያናጋል የሚሉት ተቃዋሚዎች፣ የኬንያ መንግስት ያስበውን የታክስ ጭማሪ እንዲተወው ለሳምንታት በዘለቀ ተቃውሞ ጠይቀዋል፡፡
መንግስት ተቃውሞ የበረታበትን አዲስ የፋይናንስ ህግ ተፈጻሚ እንደማያደርግ ቢያሳውቅም ፕሬዝዳንቱ ስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቁ ድምጾች በርትተው ሰንብተዋል፡፡
ተቃውሞውን ተከትሎ 39 ሰዎች ሶሞቱ 361 የሚሆኑት ደግሞ መካከለኛ እና ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሀገሪቱ ሰበአዊ መብት ኮሚሽን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
ኬንያ ለመጨረሻ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ካቢኔዋን የበተነችው በ2005 በፕሬዝዳንት ሙዋይ ኪባኪ የስልጣን ዘመን ነበር።