በኬንያ የመንግስት ተቺዎች በህገ ወጥ መንገድ መታፈንን የሚቃወሙ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው
የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እስካሁን 89 የመንግስት ተቃዋሚዎች መታፈናቸውን አስታውቀዋል
ከአርብ ጀምሮ አፈናውን በመቃወም ሰልፎች ሲደረጉ የቆዩ ሲሆን በዛሬው ዕለት ሲካሄድ የነበረ ሰልፍም በፖሊስ ተበትኗል
የኬንያ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ ጠበቆች እና ፖለቲከኞች በመንግስት ተቺዎች ላይ ያነጣጠረ አፈና መበራከት እንዲቆም በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡
የጸጥታ ሃይሎች በሰኔ እና በሐምሌ ወር በወጣቶች በተመራው መንግስትን በሚቃወሙ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ የተሳተፉ ሰዎችን በማደን ህገ-ወጥ እስራት ፈጽመዋል በሚል ተከሰዋል።
በቅርብ ጊዜ አድራሻቸው ጠፍቷል የተባሉት ወጣቶች በዋነኛነት ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶን በበይነ መረብ ላይ የነቀፉ ወጣቶች ናቸው ተብሏል።
እነዚህ ወጣቶች ሩቶ ሞተው በአስክሬን ሳጥን ውስጥ ተኝተው የሚያሳይ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የተሰራ ምስል በማህበራዊ ሚዲያዎች አጋርተው ነበር፡፡
የኬንያ ፖሊስ እጁ እንደሌለበት ቢገልጽም የመብት ተሟጋቾች ፖሊስ በአፈናው ላይ እጁ ከሌለበት ጠፉ የተባሉትን ሰዎች ለማፈላለግ ለምን ጥረት አያደርግም በሚል ጠይቀዋል፡፡
የሀገሪቱ የህግ ማህበርም የፖሊስ አዛዦች የመንግስት ተችዎች ላይ ባነጣጠረው አፈና ካልተሳተፉ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተጠያቂ የሆኑ አካላትን በመመርመር ለፍትህ እንዲያቀርቡ አሳስቧል፡፡
በተቃውሞ ሰልፉ ምክንያት ከዊሊያም ሩቶ ጋር በተፈጠረ ግጭት ከስልጣን የተነሱት የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪጋቲ ጋቻጉዋ ከጠፉት ሰዎች ጀርባ ሚስጥራዊ የመንግስት ቡድን እጅ አለበት ሲሉ ከሰዋል፡፡
ጋቻጉዋ ባሳለፍነው አርብ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በሰጡት መግለጫ "እነዚህን ህጻናት ማፈን መፍትሄ አይሆንም፤ በዚች ሀገር ታሪክ መንግስት ህጻናት እና ታዳጊዎች ላይ ያነጣጠረ ጭቆና ሲያደርግ የመጀመሪያው ነው" ብለዋል።
የኬንያ ብሔራዊ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከሰኔ ወር ጀምሮ ማንነታቸው ባልታወቁ የመንግስት ሀይሎች 82 ሰዎች መታፈናቸውን ገልጾ 29ኙ አሁንም የት እንዳሉ እንደማይታወቅ አመላክቷል፡፡
የኬንያ የፍትህ አካላት በበኩላቸው አፈናዎች ህጋዊ መሰረት የሌላቸው እና የዜጎችን መብት አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶች ናቸው ሲሉ አውግዘዋል፡፡