የኬንያው ፕሬዝዳንት ተቃውሞ የበረታበትን የፋይናንስ ህግ ውድቅ አደረጉ
ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በሰጡት መግለጫ፥ “ህዝቡ ጮክ ብሎ ያሰማውን ተቃውሞ በማድመጥ የፋይናንስ ህጉ ላይ ላለመፈረም ወስኛለሁ” ብለዋል
ተቃዋሚዎች ግን ከ23 በላይ ኬንያውያን የተገደሉበት ህዝባዊ ተቃውሞ እንዲቀጥል ጥሪ እያቀረቡ ነው
ኬንያ ተቃውሞ የበረታበትን አዲስ የፋይናንስ ህግ ተፈጻሚ እንደማታደርግ ገለጸች።
ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከጥቂት ስአታት በፊት በሰጡት መግለጫ፥ በሀገሪቱ ፓርላማ በትናንትናው እለት በጸደቀው ህግ ላይ ፊርማቸውን እንደማያኖሩ ተናግረዋል።
“ህዝቡ ከፋይናንስ ህጉ ምንም እንደማይጠቀም ጮክ ብሎ ያሰማውን ቅሬታ በማድመጥ ህጉ ላይ ፊርማዬን ላለማሳረፍ ወስኛለሁ፤ በመሆኑም ህጉ ተፈጻሚ አይሆንም” ሲሉም ገልጸዋል።
ለሳምንታት በዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ በጠፋው የሰው ህይወትና በደረሰው የንብረት ውድመት ማዘናቸውን በመግለጽም ከኬንያውያን ወጣቶች ጋር እንደሚመክሩ ጠቁመዋል።
የግብር ጭማሪ የሚያስከትለውና ኬንያ የውጭ እዳዋን ለመቀነስ የምታውለውን 2 ነጥብ 7 ቢሊየን ዶላር ያስገኛል የተባለው የፋይናንስ ህግ ውድቅ መደረጉ ለተቃውሞ አደባባይ ለወጡት ወጣቶች ትልቅ ድል ሆኗል።
ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንት ሩቶ ስልጣን እንዲለቁ የሚጠይቁ ሰልፎችን ለማድረግ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚቀርበው ጥሪ መቀጠሉን ሬውተርስ ዘግቧል።
በነገው እለትም 1 ሚሊየን ኬንያውያን አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ የማህበረሰብ አንቂዎች ጥሪ እያቀረቡ ነው ተብሏል።
የኬንያ ፖሊስ ተቃውሞውን ለማብረድ በወሰደው እርምጃ በጥቂቱ የ23 ሰዎች ህይወት ማለፉ የቀሰቀሰው ቁጣ እንዳልበረደ የተነገረ ሲሆን፥ የሀገሪቱ ፖሊስም በይፋ መግለጫ ከመስጠት ተቆጥቧል።
የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ሪጋቲ ጋቻጉዋ ወታቶች ህይወት ከሚቀጥፍና ንብረት ከሚያወድም የአመጽ እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ ጠይቀዋል።
ለመንግስት ደካማ ምክር ለግሰዋል ያሏቸውን የሀገሪቱ የደህንነት አገልግሎት ሃላፊ ስልጣን እንዲለቁም ነው ጥሪ ያቀረቡት።
ኬንያ አዲሱን የፋይናንስ ህግ ውድቅ ማድረጓ የውጭ እዳን የማቃለል አንዱ መፍትሄ ይሆናል ካላት የአለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ጋር ሊያጋጫት እንደሚችል ይጠበቃል።