ኬንያ ውጥረት የሚያረግብ የባህር ጠረፍ ስምምነት ሀሳብ ማቅረቧ ተገለጸ
ይህ የስምምነት ሀሳብ በቀጣናው ያሉ ወደብ አልባ ሀገራት ወደብ ለንግድ አላማ የሚያገኙበት አማራጭ የያዘ ነው ብለዋል ባለስልጣኑ
ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት የተፈጠረው፣ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የወደብ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟን ተከትሎ ነበር
ኬንያ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት የሚያረግብ የስምምነት ሀሳብ ማቅረቧ ተገለጸ።
ኬንያ፣ የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድን የወደብ ስምምነት ተከትሎ የተፈጠረውን ውጥረት ያረግባል ያለችውን የባህር ጠረፍ ስምምነት ሀሳብ ማቅረቧን የኬንያ ባለስልጣን መናገራቸው ተገልጿል።
በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት የተፈጠረው፣ ኢትዮጵያ ሶማሊያ የሉአላዊ ግዛቷ አካል አድርጋ ከምታያት ሶማሊላንድ ጋር የወደብ የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟን ተከትሎ ነበር።
- ኢትዮጵያ የሶማሊያን ሉአላዊነትና አለማቀፉን ህግ ጥሳለች - ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሃሙድ
- በስምምነቱ "የተጣሰ ሕግና የተሰበረ እምነትም የለም"- የኢትዮጵያ መንግስት
በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና በራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሄ አብዲ መካከል በፈረንጆቹ አዲስ አመት የተፈረመው ሰነድ፣ ኢትዮጵያ በሶማሊላንድ 20 ኪሎሜትር የሚረዝም የባህር ጠረፍ ላይ የባህር ኃይል እንድታቋቁም እና በምላሹ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና እንድትሰጥ የሚያስችል መሆኑ በወቅቱ መገለጹ ይታወሳል።
በዚህ ስምምነት ሉአላዊነቷ መጣሱን የገለጸችው ሶማሊያ ከሳምንት በፊት በሶለማሊያ ኢትዮጵያ አምባሳደር እንዲባረሩ በማድረግ ውጥረቱን ከፍ አድርጋዋለች።
የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋና ጸኃፊ ኮሪር ሲንጎይ ኬንያ አማራጭ ያለችውን የስምምነት ሀሳብ ከጅቡቲ እና የቀጣናው ሀገራት ጥምረት ከሆነው ኢጋድ ጋር እየመከረችበት ነው ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህ የስምምነት ሀሳብ በቀጣናው ያሉ ወደብ አልባ ሀገራት ወደብ ለንግድ አላማ የሚያገኙበት አማራጭ የያዘ ነው ብለዋል ባለስልጣኑ።
ባለስልጣኑ "ኢጋድ የባህር ጠረፍን በጋራ ለመጠቀም የሚያስችል ስምምነት ማዘጋጀት ይችላል" ሲሉም ተናግረዋል።
ባለፈው ሀሙስ እለት የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሀሰን ሸህ መሀመድ ከኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ ጋር ለችግሩ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ለመፈለግ በናይኖቢ ተገናኝተው መክረዋል።
ሲንጎይ "ቀጣናው የተረጋጋ እንዲሆን ከሁሉም አካላት ጋር እንነጋገራለን " ብለዋል።
ሲንጎይ እንዳሉት ኬንያ ያቀረበችው ሀሳብ ተቀባይነት ካገኘ የሶማሊያ የግዛት አንድነት ሳይጣስ ኢትዮጵያ "የተረጋጋ እና የሚተነበይ የጠረፍ ሀብት" ተጠቃሚ እንድትሆን ያስችላታል።
ኢትዮጵያ እና ሶማላያ ሀሳቡን እያጤኑት ነው ያሉት ሴንጎይ በሀሳቡ ላይ ለመነጋገር መሪዎቹ እንዲገናኙ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል ብለዋል።
አልሸባብ ግጭቱን የሞቃጂሹ መንግስት ሉአላዊነት ማስጠበቅ እንደማይችል ለማሳየት እየተጠቀመበት ስለሆነ በቶሎ መወያየት አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።