የሶማሊያ ካቢኔ በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ ወደብ ስምምነት ላይ አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ
የኢትዮጵያን ቀይ ባህርን የመጠቀም ፍላጎት የሚያሳካ የመግባቢያ ሰነድ ከሶማሊላንድ ጋር ተፈራርማለች
ሶማሊያ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ያቀረበችውን የባህር በር ጥያቄ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል
የሶማሊያ ካቢኔ በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል በተደረሰው የወደብ ስምምነት ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱ ተገለጸ።
የሶማሊያ ካቢኔ ዛሬ በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ከተገነጠለችው የሶማሌላንድ ግዛት ጋር የቀይ ባህር በርበራ ወደብ እንድትጠቀም የሚያስችላትን ስምምነት ዙሪያ ለመወያየት ውሳኔ ለማሳለፍ መሆኑን የሶማሊያ የዜና አገልግሎት አስታውቋል።
- የኢትዮጵያን ቀይ ባህርን የመጠቀም ፍላጎት ያሳካል የተባለ የመግባቢያ ሰነድ መፈረሙን መንግስት ገለጸ
- ሶማሊያ የኢትዮጵያን የቀይ ባህር ወደብ የማግኘት ጥያቄ ውድቅ ማድረጓ ተገለጸ
ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን የመጠቀም ፍላጎቷን ለማሳካት መንገድ የሚጠርግ እና የወደብ አማራጮችን የሚያሰፋ የመግባቢያ ሰነድ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ላይ ትናንት መፈራረሟ ይታወቃል።
ስምምነቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የሶማሌ ላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ በትናንትናው እለት ተፈራርመዋል።
በኢትዮጵያና እና የሶማሊላንድ መካከል የተፈረመው ስምምነት ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ በሊዝ ወታደራዊ ካምፕ እንድታገኝ እና የባህር ላይ የንግድ እንቅስቃሴ እንድታደርግ መንገድ የሚከፍት መሆኑን የጠ/ሚኒስትሩ ብሄራዊ ደህንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ተናግረዋል።
በምላሹ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንደምትወስድ የገለጹት አምባሳደር ሬድዋን ተጨማሪ ዝርዝር ግን አልሰጡም።
የሶማሊያ ካቢኔ በዛሬ ስብሰባው በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ ወደብ ስምምነት ላይ ምላሽ እንደሚሰጥ የሶማሊያ የዜና አገልግሎት (ሶና) ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከወራት በፊት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት እና ጥያቄውን ለጎረቤት ሀገራት ማቅረባቸው ይታወሳል።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ጥሪ ውድቅ ካደረጉ ሀገራት መካከል ሶማሊያ አንዷ ስትሆን፤ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "የሶማሊያ ሉአላዊነት እና የግዛት አንድነት- መሬት፣ ባህር እና አየር- ቅዱስ እና ለድርድር የማይቀርቡ ናቸው" ብሎ ነበር።