በምርጫው ውጤት ቅሬታ በመቅረቡ ጉዳዩን የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያየዋል
በኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለ5ኛ ጊዜ በዕጩነት የቀረቡት ራይላ ኦዲንጋ የምርጫውን ውጤት ቅሬታ ወደ ፍርድ ቤት ሊወስዱ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኬንያ ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን ትናንት ዊሊም ሳሞይ ሩቶ ማሸነፋቸውን ይፋ ቢያደርግም ኦዲንጋ ግን ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ወስነዋል። ራይላ ኦዲንጋ ከምፈርጫው ውጤት መገለጽ በኋላ ትናንት ለመጀመሪያ አስተያየት ሰጥተዋል።
ራይላ የኬንያ ፕሬዝዳነት ለመሆን 5 ጊዜ ቢወዳደሩም በምርጫው መሸነፋቸው ተገልጿል።
የ 77 ዓመቱ ራይላ ኦዲንጋ በሀገሪቱ የተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ተቀባይት እንደሌለው ገልጸዋል።በፓርቲያቸው የሚዲያ ክፍል ትናነት በሰጡት መግለጫ ውጤቱን ተቀባይነት የለውም ያሉ ሲሆን ጉዳዩንም ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱ ተናግረዋል።
በምዕራብ ኬንያ በምትገኘው ኪሱሙ ከተማ የሚገኙ የኦዲንጋ ደጋፊዎች “ኦዲንጋ ለምን ተሸነፉ” በሚል ጎማ እያቃጠሉና ተቃውሚ እያሰሙ ናቸው።
የአዛውንቱ ደጋፊዎች በኪሱሙ እና በሌሎች አካባቢዎች “ካለ ኦዲንጋ ሰላም የለም” እያሉ ነው።
የቀድሞዋን የሀገሪቱን ፍትህ ሚኒስትር እና የኦዲንጋ ምክትል ማርታ ካሩዋ የምርጫው ውጤት በሂሳብ ስሌት እስካሁን ያልነበረ እንደሆነ ገልጸዋል።
በምርጫው ተገኝቷል የተባለው ውጤት ሲደመር የሚመጣው 100 በመቶ 100 የሚል ቁጥር ሳይሆን 100 ነጥብ 01 በመቶ ሆኗል።
አራት የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን አባላት የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤትን እንደማያጸድቁ መግለጻቸውንም ኦዲንጋ በአብነት አንስተዋል።
ሁለት የምርጫ ኮሚሽን አባላት ደግሞ ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል። የ 77 ዓመቱ ፕሬዝዳንታዊ እጩ በምርጫው አሸንፈው ስልጣን ከያዙ በኬንያ ታሪክ የመጀመሪያዋን ሴት ምክትል ፕሬዝዳንት እንደሚሾሙ ቃል ገብተው ነበር።
በኬንያ የተካሄደውን ምርጫ የተቃወሙት ኦዲንጋ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ከወሰዱት፤ ፍርድ ቤት ጉዳዩን አይቶ ወይ ምርጫውን ያጸድቀዋል አሊያም ምርጫውን ውድቅ ያደርገዋል።
ምርጫው ውድቅ የሚደረግ ከሆነ በሀገሪቱ በድጋሚ ምርጫ ይደረጋል።ምርጫው ወድድ ካልተደረገና የሩቶ አሸናፊነት ከጸደቀ አሸናፊው ከሁለት ሳምንት በኋላ ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ።