የኬንያ ፍርድ ቤት የራይላ ኦዲንጋን ክስ ውድቅ አደረገ
የኬንያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በኬንያ በተካሄደው ፕሬዝዳናታዊ ታዊ ምርጫ የዊሊያም ሩቶ አሸናፊነትን አፀና።
በኬንያ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ለ5ኛ ጊዜ በዕጩነት የቀረቡት ራይላ ኦዲንጋ የምርጫውን ውጤት አልቀበልም በማለት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደው ነበር።
የሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዛሬው እለት ጉዳዩ ላይ ብይን የሰጠ ሲሆን፤ በዚህም የራይላ ኦዲንጋን ክስ ውድቅ ማድረጉን አስታቋል።
ፍርድ ቤቱ ቀደም ብሎ በሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን አሸናፊ የተባሉት ዊሊያም ሩቶ የሀገሪቱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት መሆናቸን የሚያሳየውን ውጤት አጽንቷል።
ይሀንን ተከትሎም ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሪቱ የፊታችን መስከረም 3 ቃለ መሃላ እንደሚፈፅሙ ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
ኬንያዊያን ባገባደድነው ነሃሴ ወር ላይ ፕሬዝዳንታቸውን ለመምረጥ ድምጽ ሰጥተው ነበር።
ይህንን ተከትሎም በሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ 50 ነጥብ 49 የሚሆነውን የመራጮች ምርጫ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸው መገለጹ ይታወሳል።
ሆኖም ግን የ 77 ዓመቱ ራይላ ኦዲንጋ በሀገሪቱ የተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤት ተቀባይት እንደሌለው በመግለጽና “አልተሸነፍኩም” በሚል የፍርድ ቤት ደጃፍ ላይ ደርሰዋል።
ኦዲንጋ በመከራከሪያነት ያነሱት፤ አራት የምርጫ ኮሚሽን አባላት የምርጫ ውጤቱን አናጸድቅም ብለዋል ማለታቸው እና የውጤቱ ድምር 100 ነጥብ 01 መምጣቱን ነው።
የኬንያ ፍርድ ቤት ከኦዲንጋ የቀረበለትን ቅሬታ በመመልከት ነው የዊሊያም ሩቶን አሸናፊነት ያፀናው።