“ተሸናፊው” ኦዲንጋ ያቀረቡት ቅሬታ በሁለት ሳምንት ውስጥ ይታያል
የኬንያ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዕጩ ራይላ ኦዲንጋ “ምርጫው ተጭበርብሯል” ያሉበትን ማስረጃ በመኪና ጭነው አቀረቡ፡፡
የኬንያ ምርጫ ኮሚሽን በሀገሪቱ የተካሄደውን ምርጫ ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ ማሸነፋቸውን ይፋ ቢያደርግም ራይላ ኦዲንጋ ግን ውጤቱን እንደማይቀበሉት ገልጸው ነበር፡፡ ከዚህ ባለፈም ምርጫው መጭበርበሩን በመግለጽ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስዱት ገልጸው ነበር፡፡
በዚህም መሰረት በምርጫ ኮሚሽኑ “ተሸንፈዋል” የተባሉት ራይላ ኦዲንጋ በአንድ የጭነት መኪና ውስጥ የተከማቹ ማስረጃዎችን ዛሬ ለሀገራቸው ፍርድ ቤት አቅርበዋል፡፡ የጭነት መኪናው የኦዲንጋን ማስረጃዎች ይዞ ወደ ፍርድ ቤት ሲገባ ደጋፊዎቻቸው ከበዋቸው ነበር ተብሏል፡፡
ከኦዲንጋ ጋር የተወዳደሩትና ምክትል ፕሬዝዳንት ሊሆኑ የነበሩት የቀድሞዋ የፍትህ ሚኒስትር ማርታ ካሩዋ እና ጠበቆቻቸው ማስረጃዎችን አደራጅተዋል ነው የተባለው፡፡ ጀምስ ኦሬንጎ የተባሉት የራይላ ኦዲንጋ ጠበቃ “ሀገራችንን ባርክል ፍትህ የእኛ ጠበቃ ነው” የሚል ጹሑፍን አስፍረዋል፡፡
22 ሚሊዮን ኬንያዊያን በዚህ ዓመት በተካሄደው ምርጫ ድምጽ ለመስጠት ተመዝግበው ነበር፡፡
በውጤቱም ዊሊያም ሳሞይ ሩቶ 50 ነጥብ 49 የሚሆነውን የመራጮች ምርጫ ድምጽ በማግኘት ማሸነፋቸው ቢገለጽም ኦዲንጋ ግን “አልተሸነፍኩም” በሚል የፍርድ ቤት ደጃፍ ላይ ደርሰዋል፡፡
ኦዲንጋ በመከራከሪያነት ያነሱት፤ አራት የምርጫ ኮሚሽን አባላት የምርጫ ውጤቱን አናጸድቅም ብለዋል ማለታቸው እና የውጤቱ ድምር 100 ነጥብ 01 መምጣቱን ነው፡፡ የኬንያ ፍርድ ቤት ከኦዲንጋ የቀረበለትን ቅሬታ በሁለት ሳምንት ውስጥ እንደሚመለከት ይጠበቃል፡፡