ኬንያ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ላልተከተቡ ዜጎች አገልግሎት መስጠት እንደምታቆም ገለጸች
እስከ ታህሳስ አጋማሽ ድረስ የኮሮና ቫይረስ ክትባት እንዲወስዱ የኬንያ ጤና ሚኒስቴር አሳስቧል
ያልተከተቡ ዜጎች ጤናን ጨምሮ ሌሎች መንግስታዊ አገልግሎቶችን እንደማያገኙ ተገልጿል
ኬንያ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ላልተከተቡ ዜጎች አገልግሎት መስጠት እንደምታቆም ገለጸች፡፡
የኬንያ ጤና ሚኒስትር ሙታሂ ካግዌ በሰጡት መግለጫ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ያልወሰዱ ዜጎች ጤናን ጨምሮ ሌሎች መንግስታዊ አገልግሎቶችን እንደማያገኙ ተናግረዋል፡፡
ዜጎች አነዚህን አገልግሎቶች ለማግኘት እስከ ታህሳስ አጋማሽ ቀናት ድረስ ወይም በአንድ ወር ውስጥ እድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ የሆኑ ሁሉ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባቶችን እንዲከተቡ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡
ክትባቱን ላልወሰዱ ዜጎች ከሚከለከሉ አገልግሎቶች መካከል ትምህርት፣የዜግነት አገልግሎቶች፣ጤና፣ የታሰሩ ሰዎችን መጠየቅ፣ የወደብ እና የፖስታ ቤት አገልግሎቶች ዋነኞቹ ናቸው፡፡
ኬንያ አገር አቀፍ የክትባት ዘመቻዎችን ከዚህ ሳምንት ጀምሮ መስጠት እንደምትጀምር የገለጸች ሲሆን በዚህ የአንድ ወር ዘመቻ 30 ሚሊዮን ዜጎቿን ለመከተብ ማቀዷን ገልጻለች፡፡
በኬንያ 255 ሺህ ዜጎች በኮሮና ቫየረስ የተጠቁ ሲሆን ከ5ሺህ 300 በላይ የሚሆኑት ደግሞ በዚሁ ቫይረስ ምክንያት ህይወታቸውን እንዳጡ የአፍሪካ ሲዲሲ መረጃ ያስረዳል፡፡