በኬንያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 4 ከፍ ብሏል
በኬንያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 4 ከፍ ብሏል
ኬንያ ቫይረሱ ወደ ሀገሪቱ መግባቱ ከተረጋገጠበት ባለፈው አርብ ጀምሮ እስከአሁን ድርስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 4 መድረሱን አስታውቃለች፡፡
በዛሬው እለት ደግሞ በአንድ የግል የህክምና ማእከል በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው መገኘቱን የኬንያን የጤና ካቢኔ ጸኃፊ ሙታሂ ካግዌን ጠቅሶ የሀገሪቱ ጋዜጣ ዴይሊ ኔሽን ዘግቧል፡፡
ታማሚው በሰኔ 30፣ 2012 ከሎንደን ወደ ኬንያ መምጣቱን የገለጹት ካግዌ ከታማሚው ጋር ንክኪ የነበራቸውን ሰዎች የመፈለጉ ስራም እየተሰራ መሆኑንን ተናግረዋል፡፡
እስካሁን ኬንያ 111 የኮሮና ቫይረስ ምርመራዎችን አካሂዳለች፡፡ ከተመረመሩት መካከል 71 ሰዎች ከቫይረሱ ነፃ፣36ቱ በህምና በክትትል ላይ ሲሆኑ 4ቱ በቫይረሱ እንደተያዙ መረጋገጡን ጸኃፊዋ አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው እሁድ እለት ተጨማሪ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውን ፕሬዘዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አስታውቀው ነበር፡፡ ፕሬዘዳንቱ መማር ማስተማር በሁሉም ደረጃ ለጊዜው እንዲቆም ማዘዛቸውም ይታወሳል፡፡
ኮሮና ቫይረስና ምስራቅና አፍሪካ
ኮሮና በምስራቅ አፍሪካ አድማሱን አስፋፍቶ እስከዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ፣ በሱዳን፣ በኬንያ፣ በታንዛኒያና በሶማሌያ መግባቱ ተረጋግጧል፡፡ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መጋቢት 4፣ 2012 በሰጡት መግለጫ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው መኖሩን ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
ኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ
ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት መጋቢት 4፣ 2012 በሰጡት መግለጫ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው መኖሩን ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
ግለሱቡ ጃፓናዊ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ የገባው የካቲት 25 መሆኑንና ከእሱ ጋር ንክኪ ያላቸው 25 ሰዎች ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ እስካሁን በቫይረስ ተያዙ ሰዎች ቁጥር 5 ደርሷል፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ዛሬ ባወጣው ዛሬ መግለጫ “በሽታውን ሪፖርት ከተደረገባቸው አገራት የመጡ ተጓዞችን በተጨማሪ በኮረና ቫይረስ መያዛቸውን ማረጋገጥ ከተቻለው 5 ግለሰቦች ጋር የቅርብ ንክኪ ያላቸውን ዘጠኝ መቶ ዘጠና ሁለት (992) ባሉበት ቦታ ለ14 ቀናት የሚደረግ የጤና ክትትል እየተደረገላቸው የሚገኙ ሲሆኑ በአሁኑ ሰዓት አንድ ሺ ሁለት መቶ ሰማንያ አምስት (1285) የሚሆኑት ደግሞ ለ 14 ቀን የጤና ክትትል ሲደረግላቸው ቆይተው ጤንነታቸው በመረጋገጡ የጤና ክትትላቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡”
“በሽታው ተመሳሳይ ምልክቶች በማሳየታቸው እንዲሁም ከመጀመሪያው ታማሚዎች ጋር ንክኪ የነበራቸውን ጨምሮ በአሁኑ ሰዓት አንደ መቶ አስራ ሰስት (113) ተጠርጣሪዎች በተለያየ ጊዜ በለይቶ መቆያ ማእከል እንዲቆዩና የላብራቶሪ ምርመራ ውጤታቸው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው በመረጋገጡ ሰባ አራቱ (74) ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ተደርጓል፤ አምስቱ ( 5) የኮሮና ቨይረስ የተገኘባቸው ታማሚዎች ሲሆኑ በለይቶ ማቆያ የህክምና መስጫ ማዕከል የቅርብ የሕክምና ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡ ሰላሳ አራቱ (34 ) ተጠርጣሪዎች በለይቶ ማቆያ ሆነው የለቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡”
ከቻይና ውሀን ግዛት የተነሳው የኮሮና ቫይረስ መላው ዓለምን አዳርሷል፡፡ ቫይረሱ እስካሁን ከ5,000 በላይ ለሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት ሲሆን 170,000 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ተይዘዋል፡፡