የኬንያና ሶማሊያ መሪዎች “በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ”ለመተባበር መስማማታቸውን ገለጹ
መሪዎቹ ቀደም ሲል የተደረሰው “የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነት” ለማጠናከር ተስማምተናል ብለዋል
ሀሰን ሼክ መሀሙድ “ የሀገራቱ ትስስር የሚጠናከረው በጋራ ወደፊት ስንራመድ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ”ብለዋል
የኬንያና ሶማሊያ መሪዎች በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት መስማማታቸውን ገለጹ፡፡
በትናንትናው እለት የመሪነት በትረ ስልጣን የጨበጡት አዲሱ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ፤ የሶማሊያ አቻቸውን ሀሰን ሼክ መሀሙድን በቤተ መንግስት (የኬንያ ስቴት ሃውስ) ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
ዊልያም ሩቶ ከሀሰን ሼክ መሀሙድ ጋር በነበራቸው ውይይት ሀገራቱ ለጋራ ጥቅም በትብብር መስራት በሚችሉባቸው መስኮች ላይ መምከራቸው ገልጸዋል፡፡
በሁለቱም ሀገራት ቀደም ሲል የተዋቀረው የጋራ የትብብር ኮሚሽን አፈጻጸም በቅርበት ለመከታተል ከስምምነት ደርሰናል ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ፤ የኮሚሽኑን ስራዎች በቅርበት መከታተል ሀገራቱ ከወራት በፊት የተፈራረሙት “ የንግድ ስምምነት” እንዲጠናከር የሚያደረግ ነው ብለዋል፡፡
የሶማሊያ-ኬንያ ግንኙነት በበርካታ ቀጠናዊ ተግዳሮቶችና እድሎች የተቆራኘ ነው ያሉት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በበኩላቸው፤ ሀገራቱ ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸው ለማሳደግ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ “በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ትስስር ይበልጥ የሚጠናከረው በጋራ ወደፊት ስንራመድ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ”ም ብለዋል፡፡
በተጨማሪም መሪዎቹ “በሶማሊያ ያለውን የጸጥታ ሁኔታና የቀጠናው ሰላም እንዲረጋጋ” በማድረግ ረገድ በትብብር ለመስራት መስማማታቸው የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ አስታውቋል፡፡
ኬንያና ሶማሊያ በንግድና የዲፕሎማሲ ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት የተፈራረሙት ከሁለት ወራት በፊት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ስምምነቱ የተፈረመው በቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ነበር፡፡
ሁለቱ ሀገራት የተፈራረሙት የንግድ ስምምነት፤ ሶማሊያ ወደ ኬንያ ዓሳ መላክ እንድትችል እንዲሁም ኬንያ ወደ ሶማሊያ ጫት መላኳን እንድትቀጥል የሚያስችል ነው።
የኬንያ አየር መንገድ ወደ ሞቃዲሾ የሚያደርገው በረራም ቀደም ሲል በነበረው የአየር ትራፊክ ስምምነት መሰረት እንደሚቀጥል የገለጸበትም ነበር ስምምነቱ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ ወደ ስልጣን በመጡት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ የሹመት ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ "ሰላምና የበለጸገች የሶማሊያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ማየት የሁሉም ኬንያዊ ህልም ነው" ሲሉ ለሶማሊያ ያላቸውን መልካም ምኞት መግለጻቸው አይዘነጋም።
የአሁኑ የፕሬዝዳንት ሩቶ እና ሼክ መሀሙድ ስምምነት በቅርቡ የተጀመረውን መልካም የሚባል የሁለትዮሽ ወደ ተሻለ ደረጃ ያደርሰዋል ተብሎ እንደሚታመን የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡
ኬንያ እና ሶማሊያ ለረዥም ጊዜያት በዘለቀ “የድንበር ውዝግብ” ውስጥ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡