የሶማሊያ ህዝብ ከአል ሸባብ ጋር ለሚደረግ 'ሁለንተናዊ ጦርነት' እንዲዘጋጅ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ጥሪ አቀረቡ
ሐሰን ሼክ ማህሙድ አል ሸባብን ለማስወገድ የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ ቃል ገብተዋል
ሰሞነኛውን ጥቃት የተመለከተ መግለጫ አውጥተዋል
የሶማሊያ ህዝብ ከአል ሸባብ ጋር ለሚደረግ 'ሁለንተናዊ ጦርነት' እንዲዘጋጅ የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ጥሪ አቀረቡ።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ማህሙድ አሸባሪውን ቡድን ለማጥፋት ቃል ገብተዋል። ይህን ለማድረግ የሚያስችል 'ሁለንተናዊ' እርምጃ ለመውሰድ ቃል የገቡም ሲሆን ሶማሊያውያን እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል።
ሼክ ማህሙድ ሰርጎ ገቦቹን ለማስወገድ 30 ሰዓታትን ከፈጀው የሐያት ሆቴል የአል ሸባብ ጥቃት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት መግለጫ ነው ጥሪውን ያቀረቡት።
ጥቃቱ እርሳቸው ስልጣን ከያዙበት ካሳለፍነው ወርሃ ግንቦት ወዲህ፤ በቡድኑ የተፈጸመ ከባዱ ጥቃት ነው። ይህም ላለፉት 15 ዓመታት በሃገሪቱ ሲንቀሳቀስ የቆየውንና የአል ቃይዳ የሽብር ክንፍ የሆነውን ቡድን ለማስወገድ የሚደረጉ ጥረቶች ምን ያህል ፈታኝ እንደሆኑ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
ሆኖም "የሶማሊያ ህዝብ ምን ያህል በማያባራ ሀዘን እንደተሰላቸ እና በእያንዳንዱ የአሸባሪዎቹ ጥቃት ምን ያህል የሚወዳቸውን በርካታ ሰዎች እንዳጣ አውቃለሁ" ያሉት ፕሬዝዳንት ማህሙድ 'ልናጠፋው ቆርጠን ተነስተናል' ብለዋል።
"ለሰላማችን ፀር ከሆኑ ርህራሄ - አልባዎች ጋር ለምናደርገው ሁለንተናዊ ጦርነት ተዘጋጁ" ሲሉም ነው ለሶማሊያውያን ጥሪ ያቀረቡት።
ሐያት ሞቃዲሾ ከሚገኙ ታዋቂ የሃገሪቱ ሆቴሎች መካከል አንዱ ነው። ጥቂት የማይባሉ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ጭምር ለስብሰባና ለተለያዩ ግልጋሎቶች ይመርጡታል። ይህም አልሸባብ የጥፋት ዐይኑን እንዲጥልባት ምክንያት መሆኑም ነው የሚነገረው። ባሳለፍነው አርብ ወደ ሆቴሉ ሰርጎ የገባ አንድ የቡድኑ ታጣቂ በሆቴሉ መሽጎ በፈፀመው ጥቃትም በትንሹ 21 ሰዎች ሞተዋል። 117 ሰዎች ደግሞ ተጎድተዋል። ከሟቾቹ መካከል አንዱ ኖርዌያዊ ነው።
ታጣቂው ከፊል የሆቴሉን ግንባታ አፍርሰው በገቡ የሃገሪቱ ኮማንዶዎች እስኪገደል ድረስም 30 ያህል ሰዓታትን እየተዋጋ ቆይቷል።
ይህን ተከትሎም ፕሬዝዳንት ማህሙድ ትናንት ማክሰኞ የሃገሪቱን ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ስብሰባ ጠርተው አወያይተዋል። በውይይቱ የሃገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ የሃገር ውስጥ ደህንነት፣ የውጭ ጉዳይና የመከላከያ ሚኒስትሮች ተገኝተው ነበር።
ሼክ ማህሙድ፤ ፋርማጆን የተኩበትን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸንፈው ወደ ስልጣን ሲመጡ ቡድኑን ከድርጊቶቹ ለመግታት ከወታደራዊ እርምጃዎች የተለየ አካሄድን መከተል ይገባል ብለው እንደነበር ይታወሳል።
መንግስታቸው "ጊዜው ሲደርስ ብቻ" ከአል ሸባብ ጋር ሊደራደር እንደሚችልም ነበር በወቅቱ የገለፁት።
አል ሸባብ በቅርቡ በሱማሌ ክልል በኩል ወደ ኢትዮጵያ ሰርጎ በመግባት ጥቃት ለመፈጸም ያደረገው ሙከራ ከሽፎ መደምሰሱን መንግስት ማስታወቁ አይዘነጋም።