ኬንያ ለሁሉም ዜጎች ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልክ ልታዳርስ መሆኗን ገለጸች
ሀገሪቱ የበይነ መረብ አሰራሮችን ለማዘመን በ40 ዶላር ሂሳብ ለሁሉም ዜጎች ስልክ የማዳረስ ግብ አስቀምጣለች
ሶስት የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ስልክ ገጣጥመው ለማቅረብ ውል ገብተዋል
ኬንያ ዘመናዊ ስልኮችን ለዜጎቿ የማዳረስ እቅዷን በዚህ ወር እንደምትጀምር ገለጸች።
ጎረቤት ሀገር ኬንያ አገልግሎቶችን በበይነ መረብ ለማቀላጠፍ በሚል ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ለሁሉም ዜጎች የማድረስ ግብ ማስቀመጧን አስታውቃለች።
የሀገሪቱ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚንስትር ኢልውድ ኦዋሎ እንዳሉት እስከ ያዝነው ጥቅምት ወር መጨረሻ ወር ድረስ ዘመናዊ ስልኮችን ለዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ ይቀርባሉ ብለዋል።
አንድ ስልክ በ40 ዶላር ለሽያጭ ይቀርባል የተባለ ሲሆን ስልኮቹን ሶስት ኩባንያዎች ገጣጥመው ለገበያ እንደሚያቀርቡ ተገልጿል።
ሳፋሪ ኮም፣ ሸንዘን ቴሌ፣ እና ጃሚ ቴሌኮሙንኬሽን የተሰኙ ኩባንያዎች ስልኮቹን የሚገጣጥሙ ኩባንያዎች ሲሆኑ መንግሥት ለኩባንያዎቹ የገንዘብ ድጎማ አድርጓልም ተብሏል።
መንግሥት ይህን እቅድ ያወጣው የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ ተሳትፎ ከማሳደግ ባለፈ የዜጎችን የአገልግሎት ፍላጎት ለማዘመን እንደሆነ አስታውቋል።
ለኬንያውያን በመንግስት ድጎማ የቀረቡት ተንቀሳቃሽ ስልኮች አራተኛ ትውልድ ኔትወርክ ወይም 4ጂ ቴክኖሎጂ የሚሰጡ እና የተለያዩ አገልግሎቶችን በበይነ መረብ አማካኝነት ማግኘት የሚያስችሉ ናቸውም ተብሏል።
ኬንያ የተጠቀሱትን ተንቀሳቃሽ ስልኮች ታህሳስ ላይ ለዜጎች በስፋት የማዳረስ እቅድ ይዛ የነበረ ቢሆንም በምርቶቹ ጥራት እና ደህንነት ላይ ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ወደ ጥቅምት አራዝማለች።