ኬንያ ከውጭ በሚገባ በቆሎ ላይ ስትጥለው የነበረውን ቀረጥ አነሳች
የምግብ እጥረት የተጋረጠባቸው የኬንያ ዜጎች ቁጥር ወደ 4ነጥብ1 ሚሊዮን ከፍ ብሏል
የኬንያ መንግስት ቀረጡን ያነሳው በኑሮውድነት የተጎዳውን የምግብ ዋስትና ለማጎልበት መሆኑን ገልጿል
የኬንያ መንግስት በድርቅና በኑሮ ውድነት ምክንያት የተጎዳውን የምግብ ዋስትና ለማጎልበት ከውጭ በሚገባ በቆሎ ላይ የምትጥለውን ቀረጥ ማንሳቷን አስታውቃለች።
የመንግስት ቃል አቀባይ ሳይረስ ኦጋና እንደተናገሩት፥ ከውጭ በሚገባው በቆሎ ላይ ሲጣል የነበረው ቀረጥ የተቋረጠው ለብዙ አባወራዎች ዋና የሆነውን የእህል አቅርቦት ለማረጋጋት ነው።
ኦጋና እንዳሉት መንግስት በበቆሎ እና ሌሎች እንደ ስንዴ እና ሩዝ ያሉ ዋና ሰብሎችን በማስፋፋት ሐምግብ እጦት ዘላቂ መፍትሄ ማፈላለግ ጀምሯል ብለዋል።
የምግብ እጥረት የተጋረጠባቸው የኬንያ ዜጎች ቁጥር ወደ 4ነጥብ1 ሚሊዮን ከፍ ብሏል፤ ከጥቂት ወራት በፊት 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን የነበረው ቁጥር 4 ነጥብ1 ሚሊዮን መድረሱን መንግስት አስታውቋል።
ኦጋና ለአሁኑ የኬንያ የምግብ እጥረት ተደጋጋሚ ድርቅ፣ የበረሃ አንበጣ፣ የዩክሬን ቀውስ፣ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ መቆራረጥ እና በአለም አቀፍ የፋይናንስ ገበያዎች ውስጥ ያለው ተለዋዋጭነትን በምክንያትነት አስቀምጧል።
የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ለማሟላት ኬንያ ሁለት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሰንዴ ለማስገባት ሀገራትን መለየቷን የገለጹት ቃልአቀበዩ የበቆሎ፣ የስንዴ፣ የዳቦና የሌሎች የምግብ ፍጆታዎች የችርቻሮ ዋጋ ይቀንሳል የሚል ተስፋ አለኝ ብለዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም መንግስት የሰብል ምርትን፣ የምግብ ዋስትናን እና የገጠርን ገቢ ለማሳደግ በድጎማ የሚቀርብ ማዳበሪያና ሌሎች የእርሻ ግብአቶችን እንደሚያከፋፍል አስታውቋል።