ኡሁሩ ኬንያታ ወንዶች በድብቅ ከሚያፈቅሯቸው ሴቶች ይልቅ ለሚስቶቻቸው ትኩረት እንዲሰጡ ጠየቁ
ወንዶች በድብቅ ወዳፈቀሯቸው ሴቶች መሄዳቸውን ማቆም አለባቸው
ወንዶች ለቤተሰባቸው ጊዜ መስጠት እንዳለባቸው የኬንያው ፕሬዝዳንት አሳስበዋል
የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ወንዶች ከሚስቶቻቸው ውጭ የመሄድ ባህልን እንዲዲቀይሩና እንዲያቆሙ ጠየቁ።
ኡሁሩ ኬንያታ፤ በሀገሪቱ ብሔራዊ ኮንቬንሽን ማዕከል ባደረጉት ንግግር፤ ወንዶች ትኩረታቸውን ቤተሰባቸው ላይ እንዲያደርጉ የጠየቁ ሲሆን ገንዘብ ማጥፋታቸውንም ማቆም እንዳለባቸው መክረዋል።
ወንዶች ከሚስቶቻቸው ውጭ መሄድ እንዲያቆሙ ያሳሰቡት ፕሬዝዳንቱ ቤተሰብን በድህነት አስቀምጦ ከሌሎች ሴቶች ጋር መቅበጥ አስቀያሚ ድርጊት እንደሆነም ገልጸዋል።
ወንዶች ገንዘብን በብልሃት መጠቀም እንዳለባቸው የመከሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ሁሉም ማስቀደም ያለባቸው ቤተሰባቸው ላይ እንዲሆንም ጠይቀዋል።
አንዳንድ ወንዶች ከሚስቶቻቸው ውጭ በድብቅ “ጥሩ” ጊዜ ማሳለፍ እንደሚወዱ ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ይህ ድርጊት መቆም ያለበት እንደሆነም ነው በንግግራቸው ያነሱት።
አንዳንድ ወንዶች ገንዘብ ሲያገኙ በቀጥታ በድብቅ ወዳፈቀሯቸው እንስቶች እንደሚሄዱና ሁሉንም ገንዘባቸውን እንደሚያጠፉ አንስተዋል። ይህንን የሚያደርጉ ወንዶች ሚስት እንዳላቸው ሁሉ እንደሚረሱና ሙያቸውን በመጠቀም ገንዘብ ተበድረው በድብቅ ወዳፈቀሯቸው ሴቶች እንደሚሄዱ ጠቅሰዋል።
ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ወንዶች ይህንን የማይጠቅም ድርጊት በመተው፤ የወደፊት ሃላፊነታቸውን ግምት ውስጥ ያስገባ ስራ መስራት እንዳለባቸው ጠይቀዋል።
ወንዶች ቤተሰባቸውንና ልጆቻቸውን ማሰብና ለነሱ ትኩረት መስጠትን ቀዳሚ ማድረግ እንዳለባቸው ነው የገለጹት።