የጆሞ ኬንያታ ሆስፒታል ኩላሊታችንን ግዙን በሚሉ ሰዎች መማረሩን ገለጸ
ሆስፒታሉ ጥያቄው መብዛቱን ተከትሎ ኩላሊት አንገዛም የሚል ባነር ለማሰራት ተገዷል
ጆሞ ኬንያታ ሆስፒታል የኩላሊት ንቅለ ተከላ ከሚካሄድባቸው ማዕከላት መካከል አንዱ ነው
የጆሞ ኬንያታ ሆስፒታል ኩላሊታችንን ግዙን በሚሉ ሰዎች መማረሩን ገለጸ፡፡
በጎረቤት ሀገር ኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚገኘው የጆሞ ኬንያታ ሆስፒታል ኩላሊታችንን ግዙን የሚሉ ሰዎች መበራከታቸው አስታውቋል፡፡
እንደ ቢቢሲ ዘገባ ከሆነ ለተለያዩ አገልግሎቶች ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡ ሰዎች በአካል እና በሆስፒታሉ የማህበራዊ ትስስር ገጾች ሰዎች ሆስፒታሉ ኩላሊታቸውን እንዲገዛቸው ጥያቄዎችን በማቅረብ ላይ ናቸው፡፡
የሰዎች ኩላሊታቸውን የመሸጥ ፍላጎት እና ጥያቄው እየጨመረ መምጣቱን ያስታወቀው ይህ ሆስፒታል “ኩላሊት አንገዛም” የሚል ማስታወቂያ ለማሰራት መገደዱን አስታውቋል፡፡
ሆስፒታሉ ማስታወቂያውን በማህበራዊ ትስር ገጹ እና በአካል ሆስፒታሉ በር ላይ አሰርቶ በተለያዩ መንገዶች እየቀረቡለት ያሉትን የኩላሊታችንን ግዙን ጥያቄ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
የኩላሊት ንቅለ ተከላ እና ተያያዥ ህክምናዎችን እየሰጠ ያለው ይህ ሆስፒታል ኩላሊት በልገሳ መልክ ብቻ እንደሚቀበልም አስታውቋል፡፡
በኬንያ ህግ መሰረት ሰዎች የሰውነት ክፍላቸውን መሸጥ የማይችሉ ሲሆን ሰዎች በፈቃደኝነት ግን መለገስ እንደሚችሉ ይፈቀዳል፡፡
የሰዎች የኩላሊታችንን ግዙኝ ጥያቄዎች እየጨመሩ መምጣት ከምግብ እና ነዳጅ ዋጋ መጨመሩ ጋር ተያይዞ ሊሆን እንደሚችል ዘገባው አክሏል፡፡
የዓለም ባንክ ባሳለፍነው ሳምንት እንዳሳወቀው በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ክፉኛ ከሚጎዱ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ምስራቅ አፍሪካ ዋነኞቹ እንደሚሆኑ አመልክቷል፡፡