አንድ ኬንያዊ ስመ ጥር አትሌት የዶፒንግ ምርመራ ላለማድረግ ከካምፕ ማምለጡ ተገለጸ፡፡
አንድ ታዋቂ ኬንያዊ አትሌት የዶፒንግ ምርመራ ሊያደርጉ ከመጡ የጸረ-ዶፒንግ ባለሙያዎች ለማምለጥ ካምፑን ጥሎ ጠፋ፡፡
የጸረ-ዶፒንግ ቡድን አባላቱ ምዕራብ ኬኒያ ካፕሳቤት በሚባል አካባቢ ወደ ሚገኝ አንድ የአትሌቲክስ ልምምድ ካምፕ በድንገት ነበር ያመሩት፡፡
ከጥቂት ቆይታ በኋላ ወደ ካምፑ የመጡትን እንግዶች ማንነት ያጣራው አንድ ስመ-ጥር አትሌት በካምፑ ከነበረበት ቤት በመስኮት ዘሎ ከወጣ በኋላ የግቢውንም አጥር በመዝለል እግሬ አውጪኝ ብሎ አምልጧል፡፡
የኬኒያ አትሌቲክስ ዝነኛ ከመሆኑ ውጭ ማንነቱን ያልጠቀሰው አትሌቱ ቅጣት እንደሚጠብቀው ተገልጿል፡፡
የሀገሪቱ አትሌቲክስ ከፍተኛ ባለስልጣን ባርናባ ኮሪር እንዳሉት ከአበረታች እጽ ጋር በተያያዘ የጥፋተኝነት ስሜት ያላቸው አትሌቶች ከመርማሪዎች ለማምለጥ ከመሞከር ውጭ አማራጭ የላቸውም፡፡
ባለፉት 5 ዓመታት 60 የሀገሪቱ አትሌቶች ከዶፒንግ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ቅጣቶች ተጥለውባቸዋል፡፡ባለፈው ሳምንት እንኳን ከ20 ዓመት በታች የ800 ሜትር ሻምፒዩኑን አልፍሬድ ኪፕኬተርን ጨምሮ ሁለት የኬንያ አትሌቶች ከዶፒንግ ጋር በተያያዘ እገዳ ተጥሎባቸዋል፡፡
ምንጭ፡- ቢቢሲ