የኬንያ ፍርድ ቤት ካኩማ እና ዳዳብ የስደተኛ መጠለያዎችን እንዳይዘጉ አገደ
ኬንያ የስደተኛ መጠለያዎቹ ብሔራዊ የደህንነት ስጋቶቼ ናቸው በሚል ከአንድ ወር በፊት እዘጋለሁ ብላ ነበር
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን ኬንያ መጠለያዎቹን እንዳትዘጋ ተማጽኗል
ኬንያ ከአንድ ወር በፊት ሱማሊያዊያን ስደተኞች የሚጠለሉባቸውን ካኩማ እና ዳዳብ መጠለያ ጣቢያዎችን እንደምትዘጋ ማስታወቋ ይታወሳል።
አገሪቱ ከዚህ ውስኔ ላይ የደረሰችው መነሻቸውን ከስደተኛ መጠለያዎች ያደረጉ የሽብር ጥቃቶች ስጋት ስላለ መሆኑን ሲጂቲኤን አፍሪካ ዘግቧል።
የዳዳብ እና ካኩማ ስደተኛ መጠለያዎች የተሻለ ደህንነት ፍለጋ በሚል ከአገራቸው የተሰደዱ ሶማሊያዊያን መጠለያዎች ናቸው።
ኬንያ በተደጋጋሚ እነዚህን መጠለያ ጣቢያዎች የብሄራዊ ደህንነት ስጋት ምንጮች በመሆናቸው እዘጋለሁ ስትል ዓመታትን ያስቆጠረች ቢሆንም ወደ ተግባር ሳትገባ ቆይታለች።
ይሁንና እዘጋለሁ የሚለው ውሳኔ ኬንያ እና ሱማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ባቋረጡበት ወቅት መሆኑ ኬንያ ውሳኔውን እንዳለችው ልትተገብረው ትችላለች ተብሎ ነበር።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ግን የኬንያ መንግስት ውሳኔውን እንዲሰርዝ ከመጠየቃቸው ባለፈ ውሳኔው በፍርድ ቤት እንዲታገድላቸው ጠይቀው ነበር።
የኬንያ ፍርድ ቤትም መንግስት ስደተኛ መጠለያዎቹን ለመዝጋት ያስተላለፈውን ውስኔ ለጊዜው እንዲቆም ወስኗል።
ፍርድ ቤቱ ከዚህ ውስኔ ላይ የደረሰው ተጨማሪ ውሳኔዎች ያስፈልጋል በሚል ሲሆን እስከ ሀምሌ ወር ድረስ ስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎቹ እንዳይዘጉ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
በአሁኑ ወቅት በዳዳብ እና ካኩማ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከ400 ሺህ በላይ ሶማሊያዊያን በስደተኝነት ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን ሶማሊያ የገጠማት የጸጥታ ችግር ተጨማሪ ስደተኞች ወደ ኬንያ በመሰደድ ላይ እንደሆኑ ዘገባዎች በመውጣት ላይ ናቸው።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን ወቅቱ የኮሮና ቫይረስ የተስፋፋበት ወቅት በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስደተኛ ጣቢያዎቹን መዝጋት አስቸጋሪ ይህናል ብሎ ነበር።
ኬንያ የዳዳብ እና ካኩማ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን እዘጋለሁ ማለት የጀመረችው በእነደ ጎርጎሮሲያን ዘመን አቆጣጠር ከ2016 ዓመት በጋሪሳ ዩንቨርሲቲ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከተገደሉባት በኋላ ነበር።