የኬንያው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ኃላፊ በሙስና ተጠርጥረው ታሰሩ
የኬንያ ስፖርት ሚኒስቴር ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ፌዴሬሽኑን የሚመራ ተጠባባቂ ኮሚቴ አቋቁሟል
ፊፋ የኬንያ መንግስት በሀገሪቱ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የውስጥ ጉዳይ አላግባብ ጣልቃ መግባቱን ተቃውሟል
የኬንያው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኒክ ምዌንድዋ በሙስና ተጠርጥረው ዘብጥያ መውረዳቸው ተገለጸ፡፡
ፕሬዝዳንቱ የታሰሩት የኬንያ የስፖርት ሚኒስትር አሚና ሞሃመድ “ኒክን ጨምሮ ሁሉም የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች ከስራ መታገዳቸው እና ምርምራ እየተደረገ መሆኑን ማስታወቃቸውን” ተከትሎ ነው፡፡
ሚኒስትሯ ለምዌንድዋ መባረር “ፌዴሬሽኑ በመንግስት የተመደበለትን ገንዘብ ሲባክን ተጠያቂ ማድረግ አልቻሉም ” የሚል ምክንያት አቅርቧል፡፡
የስፖርት ሚኒስትሯ ተፈጸመ የተባለውን የሙስና ድርጊት እንዲጣራና ተጨማሪ ምርምራ እንዲካሄድም ለባለስልጠናት ትእዛዝ አስተላልፈዋል፡፡
የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ አመራሮች ከስልጣን መወገዳቸው ተከትሎም ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት ፌዴሬሽኑን የሚመራ ተጠባባቂ ኮሚቴ መቋቋሙንም ይፋ አድርጓል ሚኒስትሯ፡፡
የስፖርት ሚኒስትሯ አሚና እንዲህ ቢሉም ግን፤ ኒክ ምዌንድዋ ውሳኔው ትክክል እንዳልሆነና አሁን የፌዴሬሽኑ መሪ እሳቸው እንደሆኑ ሲገልጹ ተደምጠዋል፡፡
“እኛ የፌዴሬሽኑ አመራሮች በነበርንበት የኃላፊነት ቦታ መቆየት አለብን፤ እግር ኳስም በእኛ አመራር በኬንያ የሚቀጥል ይሆናል”ም ነው ያሉት ኒክ ምዌንድዋ፡፡
የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን /ፊፋ/ የኬንያ መንግስት በሀገሪቱ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የውስጥ ጉዳይ አላግባብ ጣልቃ ገብቷል በሚል እግድ እንደሚጥል ዝቷል።
የምዌንድዋ የታሰሩት የኬንያው “የሃራምቤ ስታርስ” የእግር ኳስ ቡዱን ለ2022 የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ከሩዋንዳ ጋር ግጥሚያ ለማድረግ እየተዘጋጀ ባለበት ወቅት ነው፡፡