በሃይቲ ሰላም ለማስከበር የተሰማሩ የኬንያ ፖሊሶች የስራ መልቀቂያ እያሰጉቡ እንደሚገኙ ተገለጸ
የኬንያ ፖሊሶች በደመወዝ መዘግየት ምክንያት ነው ከተልዕኮው ለመውጣት እየጠየቁ የሚገኙት

በሃይቲ የተደራጁ ቡድኖች የወንጀል እንቅስቃሴ አሁንም ተባብሶ ቀጥሏል
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሚደገፈው “የፀረ-ወንበዴ ሃይል” ሃይቲ ውስጥ ከተሰማሩት 400 ከሚጠጉ የኬንያ ፖሊሶች መካከል ከ20 በላይ የሚሆኑት ከተልዕኮው ለመሰናበት የመልቀቂያ ደብዳቤ እያሰገቡ እንደሚገኙ ተሰምቷል፡፡
ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ሶስት ፖሊሶች ለሮይተርስ እንደተናገሩት በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ ከመሆኑ ባለፈ የደመወዝ ክፍያቸው መዘግየት ከተልዕኮው ለመውጣት ጥያቄ እንዲያቀርቡ አስገድዷቸዋል፡፡
ፖሊሶቹ ጥያቄያቸውን ካቀረቡ የቆዩ ቢሆንም ለደብዳቤያቸው ምንም አይነት ምላሽ ባለማግኘታቸው በተልእኮው ማገልገላቸውን ቀጥለዋል፡፡
በተጨማሪም ከጥቅምት ወር ጀምሮ ከተልእኮው ለመሰናበት ጥያቄ ማቅረብ እንደጀመሩ፤ በህዳር ወር ብቻ 15 ፖሊሶች ለመሰናበት እንደጠየቁ እና ከነዚህ መካከል አዛዦችን ጨምሮ አምስት ከፍተኛ መኮንኖች እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡
የኬንያ ፖሊስ አዛዥ ዳግላስ ካንጃ ፖሊሶቹ እስካለፈው ጥቅምት ድረስ ደመወዝ እንደተከፈላቸው ቢናገሩም ሮይተርስ ያነጋገራቸው በስፍራው የሚገኙ ፖሊሶች ክፍያ ከተፈጸመላቸው 3 ወራት መቆጠራቸውን ተናግረዋል፡፡
2500 የፖሊስ አባላትን ከ10 ሀገራት በማሰባስብ በሃይቲ የተንሰራፈውን የወንበዴዎች ቡድን ለመከላከል በተሰማራው አለምአቀፍ ተልዕኮ ላይ ኬንያ ባሳለፍነው ሰኔ 400 ወታደሮችን በመላክ እየተሳተፈች ትገኛለች፡፡
በተደጋጋሚ የሚወጡ ዘገባዎች ተልዕኮው በገንዘብ እና በሰው ሀይል እጥረት መዳከሙን እያመላከቱ ነው፡፡
እስካሁን በተልዕኮው የሚሳተፉ ሀገራት ወደ ስፍራው የላኳቸው ፖሊሶች በጣት የሚቆጠሩ ሲሆን በጥቅምት ወር የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በሚቀጥለው ወር ተጨማሪ 600 ፖሊሶችን ለመላክ ቃል ቢገቡም እስካሁን አልተፈጸመም፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በሃይቲ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን የገደለው የወንበዴዎች ጥቃት በቅርቡ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡
የታጠቁ ቡድኖች ባለፈው ወር በዋና ከተማዋ ፖርት አው ፕሪንስ የመጨረሻዎቹን አካባቢዎች ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
በሃይቲ ላጋጠመው ነገር ዝግጁ እንዳልነበር የተናገረው አንድ የፖሊስ መኮንን "በጎዳና ላይ የሰው ሥጋ የሚበሉ ውሾች እና ሌሎች አሰቃቂ ትዕይንቶችን በማየት ፖሊሶች በስነልቦናዊ ተጽዕኖ ውስጥ እየተሰቃዩ ነው" ብሏል።
ከዚህ ባለፈም የትጥቅ አጥረት ሌላው ፈተና ሲሆን በቅርቡ የኬንያ ፖሊሶ በተቆጣጠሯቸው ቦታዎች ላይ የሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ለመቋቋም የሚያስችል በቂ ጥይት እንዳልነበራቸውም ሮይተርስ ፖሊሶችን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡