ከህወሓት ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ የአፍሪካ ህብረትን የሚደግፉ የአፍሪካ ታዋቂ ሰዎች ቢካተቱ እንደማይቃወም መንግስት አስታወቀ
መንግሥት በትግራይ ክልል መሰረታዊ አገልግሎት ለማስጀመር በቅድመ ሁኔታነት እንደማያስቀምጥ ገለጸ
መንግሥት በትግራይ ክልል መሰረታዊ አገልግሎት ለማስጀመር በቅድመ ሁኔታነት እንደማያስቀምጥ ገለጸ
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት የፌደራል መንግሥት ከህወሓት ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ የመሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመር በቅድመ ሁኔታነት እንደማያስቀምጥ ተናግረዋል።
"አገልግሎቶችን ለማስጀመር ዋናው መሰረታዊ ነገር ቅድመ ሁኔታ ሳይሆን ምክክር እና ዝርዝር ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል።
ከዚህ በፊት ትግራይ ክልልን ጨምሮ በሌሎች የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች አገልግሎቱን ማስጀመር የሚያስችል አስተማማኝ ሰላም እና መተማመን መፈጠር እንደሚያስፈልግ አምባሳደር መለስ ገልጸዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም የፌደራል መንግስት ከህወሓት ጋር በሚደረገው ድርድር ላይ በቦታ እና ጊዜ እንደማይወሰን ገልጸው በድርድሩ ላይ የአፍሪካ ህብረትን አቋም የሚደግፉ ታዋቂ አፍሪካዊያን ቢሳተፉ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃውሞ እንደሌለው አክለዋል።
መንግሥት ከህወሃት ጋር ያደርገዋል የተባለው ንግግር የሚመራው በአፍሪካ ሕብረት ብቻ እንደሆነ መግለጹ ይታወሳል።
ህወሓት በበኩሉ በቃል አቀባዩ በኩል በሰጠው መግለጫ፤ የአፍሪካ ሕብረት ከኦባሳንጆ ይልቅ፤ ኡሁሩ ኬንያታን ወይም ታቦ ኢንቤኬን ወይም ሌላ ሰው ከሰየመ ችግር እንደሌለበት ገልጿል።
ህወሓት በኬንያ ድርድር ለማድረግ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ለመላክ መዘጋጀቱን በሊቀ መንበሩ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ማስታወቁ ይታወሳል።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ በመግለጫቸው አክለውም፤ እስካሁን ባለው ጊዜ በህገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ 70 ሺህ የውጭ ሀገራት ዜጎች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በህገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የውጭ ሀገራት ዜጎችን የመመዝገብ ስራው እስከ ነሀሴ 13 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ መራዘሙ ተገልጿል።
ምዝገባው የተራዘመበት ምክንያት በቀነ ገደብ በተለያዩ ምክንያቶች ያልተመዘገቡ የዉጭ ሀገራት ዜገች ዕድሉን ለመስጠት እንደሆነም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
የውጭ ሀገራት ዜጎችን መመዝገብ ያስፈለገው ምን ያህል የውጭ ሀገራት ዜጎች በኢትዮጵያ እንዳሉ ለማወቅ እና ከተመዘገቡ በኋላ ወደ ህጋዊ መስመር ለማምጣት በማስፈለጉ ነው ተብሏል።
እስካሁን ባለው ምዝገባ ከካናዳ፣ አሜሪካ፣ ኮንጎ፣ ናይጄሪያ፣ የመን፣ ሶሪያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ቻይና፣ ኤርትራ፣ ቡሩንዲ ፣ ጋና፣ ባንግላዲሽ፣ ሕንድ፣ ላይቤሪያ፣ ካሜሮን እና ጣሊያን የመጡ ህገወጥ ዜጎች ተመዝግበዋል።