የኬንያው ፕሬዝዳንት ከኢትዮጵያ መልስ ከአሜሪካው ዲፕሎማት ማይክ ሐመር ጋር ተነጋገሩ
ዊሊያም ሩቶ ኬንያ በቀጠናው ሰላምን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል
ማይክ ሐመር አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነትን ለመደገፍ ቁርጠኛ ናት ብለዋል
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከኢትዮጵያ መልስ የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት ማይክ ሐመርን ተቀብለው አነጋገሩ፡፡
ፕሬዝዳንቱና ልዩ መልዕከተኛው የቀጠናው ሰላምና መረጋጋት በተመለከተ አንስተው መወያየታቸውንም የኬንያ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት (ኬንያ ስቴት ሃውስ) በማህበራዊ የትስስት ገጹ ባጋራው ጽሁፍ አስታውቋል፡፡
የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ፤ አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ በተለይም በኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነትን ለመደገፍ የምታደርገውን ጥረት አረጋግጠው ኬንያ በቀጠናው መረጋጋትን በማስፈን ረገድ ላደረገችው የላቀ ሚና አመስግነዋል።
ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በበኩላቸው ኬንያ በቀጠናው ሰላምን ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኝነት አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት በድርድር እንዲፈታ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ወደ ናይሮቢ፣ ፕሪቶሪያ እና አዲስ አበባ ሊጓዙ እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
በዛሬው እለት ከኬንያው ፕሬዝዳንት ጋር የተገናኙት ልዩ መልዕክተኛው ሐመር በናይሮቢ ቆይታቸው ከኬንያ መንግስት ባለስልጣናት እና ከአለም አቀፍ አጋሮች ጋር በኢትዮጵያ ሰላም ጉዳይ ይመክራሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንክን እና የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ከቀናት በፊት በነበራቸው የስልክ ቆይታ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በተመለከተ መወያየታቸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
አሜሪካ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ችግር አብቅቶ ሁሉም ወገኖች ወደ ጠረጴዛ መጥተው ለድርድር እንዲቀመጡ በአፍሪካ ህብረት በኩል እየተደረገ ያለውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ አንደሆነች በተደጋጋሚ ስትገልጽ መቆየቷ የሚታወቅ ነው፡፡
ኬንያም በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት ስትገልጽ የምትደመጥ ሀገር ናት፡፡
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በጣም እንደሚያሳስባቸው በቅርቡ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በቅርቡ ከፍራንስ-24 ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጉዳይ መፍትሄ እንዲያገኝ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉ ተሰምተዋል፡
“በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጠረው ማንኛውም ነገር ወደ ኬንያ ይደርሳል” ያሉት ዊሊያም ሩቶ፤ ግጭቱ መፍተሄ እንዲያገኝ ኬንያ የራሷን ሚና ትጫወታለችም ብለዋል፡፡
በዚህም መሰረት በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የሰላም ድርድር አፍሪካ ህብረት በአደራዳሪነት ከሰየማቸው ሶስት ግለሰቦች ኡሁሩ ኬንያታ አንዱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ቅዳሜ እና እሁድ በደቡብ አፍሪካ እንዲደራደሩ በአፍሪካ ህብረት የቀረበላቸውን ጥሪ መቀበላቸው ይታወሳል።
ነገርግን ሊካሄድ የታሰበው ድርድር በሎጂስቲክ ምክንያት መራዘሙን ሮይተርስ ዘግቧል።