አሜሪካ ለኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ደማቅ አቀባበል ለማድረግ እየተዘጋጀች መሆኗን ገለጸች
ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ግንቦት ላይ በአሜሪካ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሏል
የአሜሪካ እና ኬንያ ዲፕሎማሲ ግንኙነት የመሰረቱበት 60ኛ ዓመት በነጩ ቤተ መንግሥት እንደሚከበር ተገልጿል
አሜሪካ ለኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ደማቅ አቀባበል ለማድረግ እየተዘጋጀች መሆኗን ገለጸች።
የጎረቤት ሀገር ኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በቀጣዩ ግንቦት ወር ላይ ለይፋዊ ጉብኝት ወደ አሜሪካ እንደሚያቀኑ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም ለኬንያ አቻቸው በነጩ ቤተ መንግስታቸው ደማቅ አቀባበል ለማድረግ ዝግጅት እያደረጉ ነው ተብሏል።
ቪኦኤ የነጩ ቤተ መንግሥት ቃል አቀባይ ካሪን ፔሪን ጠቅሶ እንደዘገበው አሜሪካ እና ኬንያ ዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመሩበትን 60ኛ ዓመት ይከበራል ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን እና ዊሊያም ሩቶ በፈረንጆቹ ግንቦት 23 ቀን 2024 ላይ በነጩ ቤተ መንግስት እንደሚገናኙም ተገልጿል።
ሁለቱ ሙሪዎች በሰላም፣ ኢኮኖሚ እና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነቶችን እንደሚፈራረሙም ይጠበቃል ተብሏል።
እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ፣ ንግድ እና ቴክኖሎጂ አጀንዳዎች ዙሪያ በጋራ እንዲሰሩ የሚያደርጉ ስምምነቶችን እንደሚፈራረሙም ይጠበቃል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በ2023 በተካሄደው የአሜሪካ-አፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር በ2024 አፍሪካን እንደሚጎበኙ ተናግረው ነበር።
ይሁንና በዩክሬን እና እስራኤ ጦርነት ምክንያት እንዲሁም በቀጣዩ ህዳር በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ምክንያት የአፍሪካ ጉብኝታቸው ላይሳካ ይችላል ተብሏል።