ኬንያዊው አትሌት በካሜሮን የተካሄደ ውድድር ካጠናቀቀ በኋላ ህይወቱ አለፈ
አትሌት ኪፕሳንግ ኪፕኮሪር በሽልማት ስነ ስርዓት ላይ ተዝለፍልፎ መውደቁ ተነግሯል
የ33 ዓመቱ ኬንያዊው አትሌት ሆስፒታል ከገባ ከደቂቃዎች በኋላ ህይወቱ አልፏል
ኬንያዊው አትሌት ኪፕሳንግ ኪፕኮሪር በካሜሮን የተካሄደ የተራራ ላይ የሩጫ ውድድርን ካጠናቀቀ በኋላ ህይወቱ ማለፉን የካሜሮን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
አትሌቱ በትናንት ቅዳሜ የተካሄደውን በአፍሪካ አንጋፋው ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር የሆነው የካሜሮን የተራራ ላይ ሩጫ ካጠናቀቀ በኋላ ህይወቱ ማፉን ዢንዋ ዘግቧል።
የ33 ዓመቱ አትሌት ኪፕሳንግ ኪፕኮሪር የተራራ ላይ የሩጫ ውድድሩን በመምራት ላይ እያለ ባጋገመው የጤና እክል ምክንያት ውድድሩን ካቆመ ከደቂቃ በኋላ ተመልሶ ማጠናቀቁን የካሜሮን ደቡብ ምእራብ ክልል አስተዳዳሪ ኦካላ ባይላ ተግናረዋል።
አትሌት ኪፕሳንግ ኪፕኮሪር ውድድሩን ካጠናቀቀ በኋላ በሽልማት ስነስርዓት ላይ እያለ ተዝለፍልፎ መውደቁን የገለጹት አስተዳዳሪው ወዲያው ወደ ሆስፒታል መወሰዱን አስታውቀዋል።
ሆስፒታል ከገባ ከደቂቃዎች በኋላ ህይወቱ ማለፉንም ነው አስተዳዳሪው ኦካላ ባይላ የተናገሩት።
“ሁኔታው በጣም አሳዛኝ ነው፤ አትሌት ኪፕሳንግ ኪፕኮሪር በዚህ ውድድር ላይ ሲሳተፍ ይህ ለአራተኛ ጊዜው ነበር፤ ለአፍሪካ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ለሀገሩ ኬንያ እና ለእኛ ለካሜሩን ትልቅ ኪሳራ ነው” ብለዋል አስተዳዳሪው ኦካላ ባይላ በመግለጫቸው።
የካሜሮን የተራራ ሩጫ በርካታ አትሌቶች የሚሳተፉበት ውድድር ሲሆን፤ በዓመታዊው ውድድሩ ላይ ከኢትዮጵያ ከኮንጎ፣ፈረንሳይ፣ኬንያ፣ሊባኖስ፣ ሞሮኮ፣ ታንዛኒያ፣ ቻድ፣ ቱኒዚያ እና ካሜሩን የተውጣቱ ከ600 በላይ ሯጮች ተሳትፈዋል።
“የተስፋ ውድድር” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ውድድር አስቸጋሪ ቦታ ላይ የሚካሄድ ሲሆን፤ አትሌቶች ከባህር ጠለል በላይ ከ4,100 ሜትር በላይ ባለው ተራራ ላይ በመውጣትና በመውረድ ይወዳደራሉ።