ፑቲን ከ13 አመት በኋላ ቺቺኒያ ገቡ
ፕሬዝዳንቱ ወድ ዩክሬን የሚያመሩ የቸቸን ወታደሮችን “እናንተን ይዘን የትኛውም ሃይል አያሸንፈንም” ሲሉ አበረታተዋል
የሩሲያ አካል የሆነችው ቺቺኒያ ዩክሬንን የሚዋጉ ከ47 ሺህ በላይ ሰዎች መላኳን አስታውቃለች
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቺቺኒያ ትናንት ያልተጠበቀ ጉብኝት አድርገዋል።
ፑቲን የዩክሬን ጦር በምዕራባዊ ሩሲያ ዘልቆ ከገባ ከሁለት ሳምንት በኋላ ነው ወደ ደቡባዊ ካውካሰስ ሪፐብሊኳ ቺቺኒያ ያመሩት።
ከ13 አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በቺቺኒያ የተገኙት ፕሬዝዳንቱ ወደ ዩክሬን ለመዝመት ከተሰለጠኑ ወታደሮች ጋር ተገናኝተዋል።
ፑቲን በዚሁ ወቅት “እንደናንተ አይነት ወንዶች ይዘን በፍጹም በማንም አንሸነፍም” ማለታቸውንም ነው ክሬምሊን ያስታወቀው።
የቸቸን ወታደሮች የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል አባት ሀገራቸውን ሩሲያን ለመጠበቅ ከዚህ ቀደም ያሳዩት ወኔ እንዲደግሙትም ጥሪ አቅርበዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በሩሲያ የልዩ ሃይል ማሰልጠኛ ዩኒቨርሲቲ የተደረገውን ዝግጅት ከተመለከቱ በኋላ ከቺቺኒያው መሪው ራምዛን ካድይሮቭ ጋር መምከራቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
የፑቲን “እግረኛ ወታደር ነኝ” በሚል ደጋግሞ የሚናገረው ካድይሮቭ ቺቺኒያ በዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ 47 ሺህ ተዋጊዎችን መላኳንና ከነዚህ ውስጥ 19 ሺዎቹ በጎ ፈቃደኛ መሆናቸውን አውስተዋል።
ካድይሮቭ በአሜሪካ በሰብአዊ መብት ጥሰትና ወታደሮችን ወደ ዩክሬን በመላክ በ2020 እነ በ2022 ማዕቀብ እንደተጣለበት ይታወሳል።
ፑቲን ግን የቺቺኒያውን መሪ የጀግና ወታደሮች ተምሳሌት አድርገው ደጋግመው መጥቀሳቸውን የሩሲያው አርአይኤ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ፑቲን ቺቺኒያ ከመግባታቸው አስቀድሞ በሰሜን ኦሽቲያዋ ቤልሳን ከ16 አመት በኋላ ጉብኝት አድርገዋል።
በቤልሳን ጉብኝታቸውም ከ20 አመት በፊት የ330 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈውን የሽብር ጥቃት አውስተው “አሁንም ሽብርተኞችን እየተዋጋን ነው፤ በኩርስክ እና ዶንባስ ክልሎች” ሲሉ ተደምጠዋል።
ፕሬዝዳንቱ አሸባሪ እና ወንጀለኛ ሲሉ የገለጹትን የዩክሬን ጦር “ተገቢውን ቅጣት ማግኘቱ እንደማይቀር አትጠራጠሩ” ሲሉ መናገራቸውም ተዘግቧል።
የዩክሬን ጦር የሩሲያን ድንበር ጥሶ በመግባት ሰፊ የሞስኮን ይዝታ መቆጣጠር ከጀመረ ዛሬ 16ኛ ቀኑን ይዟል።
የሩሲያ ጦር በአንጻሩ ስትራቴጂካዊ ፋይዳዋ ከፍ ያለ ነው የተባለላትን የዩክሬን "ኒዩ ዮርክ" ከተማ መቆጣጠሩ ተገልጿል።