ስልካችን እና ኮምፒውተራችንን በስውር የሚሰልለው ”ኪሎገር”
የሳይበር ጥቃቱ በመረጃ መንታፊዎች ብቻ ሳይሆን በቅርብ ወዳጆቻችንም ሊከናወን መቻሉ አስጊነቱን ይበልጥ ጨምሮታል
ኪሎገር የምንለዋወጣቸውን መልዕክቶች፣ የምንከፍታቸውን ድረገጾች፣ የመተግበሪያዎች እና የባንኮች የይልፍ ቃላትን መዝግቦ ለጠላፊዎች ያስተላልፋል
በሳይበሩ አለም የተጠቃሚዎችን ደህንነት ጥያቄ ውስጥ ከሚከቱ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች ወይም ሶፍትዊሮች ውስጥ ኪሎገር አንዱ ነው።
ኪሎገር በኮምፒውተር ወይም ስልካችን ላይ የምናስገባቸውን ቃላት እየመዘገበ ለመረጃ ጠላፊዎች ያቀብላል።
በሁለት መልኩም የሰዎችን መረጃ እያነፈነፈ ለመዝባሪዎቹ ያስተላልፋል፤ ኮምፒውተር ላይ በሚደረግ ፍላሽ መሳይ መሳሪያ እና በተለያየ መልኩ በሚላኩ ቫይረሶች አማካኝነት እያንዳንዱን እንቅስቃሴ በጽሁፍ እየመዘገበ ይልካል።
ፋይሎችን ስናወርድ በትሮጃን መልክ አልያም ከማናውቃቸው ምንጮች የሚላኩ አጠራጣሪ ሊንኮችን ስንከፍት ኪይሎገር ወደ ስልክ እና ኮምፒውተራችን ገብቶ በስውር ስለላውን ያካሂዳል ነው የተባለው።
ደህንነቱ ያልተጠበቀ ፍለጋን ማድረግም ለዚሁ የስለላ ፕሮግራሙ ተጋላጭ ያደርጋል።
በኪሎገር የተጠቃ ሰው ምንም አይነት ሚስጢር የሚባል ነገር አይኖረውም፤ ምን ጻፍን፣ ምን አይነት ድረገጾችን ጎበኘን፣ ወደተለያዩ መተግበሪያዎች ስንገባ የምንጠቀማቸው የይለፍ ቃላት ሁሉ በኪይሎገር ይመዘገባል።
በዚህ ሶፍትዌር ጥቃት የሚደርሰው ከማይታወቁ የመረጃ መንታፊዎች ብቻ አይደለም፤ የቅርብ ጓደኞቻችንም ጥቃቱን ሊያደርሱ ይችላሉ።
ስልካችን በአጋጣሚ እጁ የገባ ሰው መተግበሪያውን አውርዶ ሊሰልለን ይችላል።
መተግበሪያው ለሚጠይቃቸው ቅድመ ሁኔታዎች አዎንታ በመስጠትም የተላላክናቸውን መልዕክቶችን፣ የባንክ የገንዘብ ዝውውር ሲደረግ የይለፍ ቃላትን ማየት፣ ያለበትን ስፍራ መለየት፣ ፎቶዎችን መመልከት ጨምሮ አጠቃላይ የስልካችን ስክሪን እንቅስቃሴ ኪሎገር እንዲመዘግብና እንዲሰልል ማድረግ ይቻላል።
የተከማቸውን መረጃም የሚሰለለውን ሰው ስልክ ዳግም በማግኘት ሙሉ በሙሉ መመንተፍ እንደሚቻል ነው ሜክ ዩዝ ኦፍ ኢት ድረገጽ ያስነበበው።
ኪሎገርን ለመልካም አላማ የሚጠቀሙበት እንዳሉ ተነግሯል።
በተለይ ወላጆች ልጆቻቸውን ለመቆጣጠር እንዲሁም መስሪያ ቤቶች ሰራተኞቻቸው ከስራ ውጭ የሆኑና የተከለከሉ ድረገጾችን እንዳይከፍቱ ለመከታተል ጥቅም ላይ ያውሉታል።
ባለሙያዎች ከኪሎገር ጥቃት ለማምለጥ ስልክን ወይም ኮምፒውተርን ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ አለመስጠት፣ የጸረ ቫይረስ መተግበሪያዎችን መጫን እና ቫይረሶችን ለማጥፋት ሁሌም ስካን ማድረግን ይመክራሉ።