የሼክ ኸሊፋ ቀጠናዊ እና አለማቀፋዊ ተጽዕኖ ምን ይመስላል?
አረብ ኤምሬትስን የአለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር ያደረጉት ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን ካረፉ ዛሬ አንድ አመት ሆኗቸዋል
የቀድሞው ፕሬዝዳንት አረብ ኤምሬትስ በአለምአቀፍ ደረጃ ትብብርና ወንድማማችነትን በመፍጠር ጉልህ አበርክቶ አላቸው
አረብ ኤምሬትስ በአለማቀፍ መድረክ ተጽዕኖዋ የጎላ ያደረጓትን መሪዋን ሼክ ካሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን አንደኛ አመት ሙት አመት በዛሬው እለት እያሰበች ነው።
ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረው የዲፕሎማሲ ስራቸው ኤምሬትስን ከአረቡ አለም ባሻገር በመላው አለም የሚያስወድስና ተደማጭ ሀገር አድርጓታል።
በእርሳቸው የስልጣን ዘመን ኤምሬትስ ከ100 በላይ የልማት አመላካቾች የቀጠናው ቀዳሚ ሀገር ሆናለች፤ በተለይም በመንግስት ላይ ባለ መተማመን እና ስራ አፈጻጸም ከፊት መቀመጥ ችላለች።
በፋይናንስ እና ግብር ጋር በተያያዙ ጉዳዮችም በ2021 ከአለም 10 ምርጥ ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ለመካተቷ የሼክ ካሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን አስተውሎት የተሞላበት መሪነት ጉልህ ድርሻ ነበረው።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቀጠናዊ እና አለማቀፋዊ ትብብር እንዲጎለብት የተጫወቱት ሚና ምን ይመስላል?
የአረብ እና የባህረ ሰላጤ (ገልፍ) ሀገራት ጋር ትብብር
ሼክ ኸሊፋ የባህረ ሰላጤው ሀገራት ሰላምና መረጋጋት ለአለም ሰላም ወሳኝ ድርሻ እንዳለው በማመን የባህረሰላጤው ሀገራት ትብብር ምክርቤት (ገልፍ ኮፐሬሽን ካውንስል) እንዲቋቋም አድርገዋል።
በዚህም የግጭት ማዕከል ተደርጎ የሚሳለውን ቀጠና በትብብር እና ልማት አስተሳስረውት የሀገራቱ ችግሮችም በጋራ ምክክር እንዲፈቱ ማድረጋቸው ነው የሚወሳው።
ኤምሬትስ የባህረ ሰላጤው ሀገራት ዜጎችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ዘርፎች በማሳተፍ በርካታ ስኬቶችን እንድትቀዳጅም የሼክ ካሊፋ ቢን ዛይድ ድርሻ በጉልህ የሚነሳ ነው።
የአረብ ሀገራት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ፈተና ሲገጥማቸውም አረብ ኤምሬትስ ቀድማ እንድትደርስ በማድረጉ ረገድ የቀድሞው መሪ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
ለአብነትም የኮሮና ቫይረስ ሲከሰት የህክማና ቁሳቁሶችን፣ ክትባት፣ ምግብ እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረስ አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
ወዳጅ ሀገራትን ማበራከት
በሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን የስልጣን ዘመን ኤምሬትስ ከቀደሙት ወዳጆቿ አሜሪካ እና ሩሲያ ባሻገር ከቻይና፣ ህንድ እና ደቡብ ኮሪያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት መስርታለች።
ከአውሮፓ ህብረት፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ጋርም የሁለትዮሽ ትብብሯን አጠናክራለች።
በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በአየር ንብረትና ታዳሽ ሃይል ልማት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ከሀገራቱ ጋር የጀመረቻቸው ትብብሮችም በአጭር ጊዜ ፍሬያማ ውጤትን አሳይተዋል።
ከ200 በላይ ሀገራት ጋር የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላት አረብ ኤምሬትስ፥ 110 ኤምባሲዎች እና 75 ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችን መክፈቷም በሼክ ካሊፋ የስልጣን ዘመን ሀገሪቱ ምን ያህል ለትብብር በሯን መክፈሯን ያሳያል።
የአለም አቀፍ እና ቀጠናዊ የፋይናንስ ተቋማት መቀመጫ የሆነችው አቡዳቢ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ከፍተኛ ሃብት እንድታገኝም ይሄው የቀድሞው መሪዋ ትብብርን ያስቀደመ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ወሳኝ ድርሻ አለው።
አለማቀፋዊ ተጽዕኖ
ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አልናህያን ኤምሬትስ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በሚደረጉ ጥረቶች ታማኝ እና ቅቡል ሀገር እንድትሆን ሰርተዋል።
ሀገራት ግጭት ውስጥ ሲገቡም ለድርድርና ሰጥቶ መቀበል ቦታ እንዲሰጡ በመወትወትና በማሸማገል ውጥረትን በፍጥነት በማርገብ ይታወቃሉ።
ይህም ኤምሬትስ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት ለሁለተኛ ጊዜ (ከ2022-2023) ጊዜያዊ አባል እንድትሆን አድርጓታል።
ሀገሪቱ የተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክርቤትን ለሶስተኛ ጊዜ (ከ2022 – 2024) መቀላቀሏም የሼክ ኸሊፋ አለማቀፋዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ሌላኛው ማሳያ ነው።
ኤምሬትስ ከ28 የመንግስታቱ ድርጅት ተቋማት ጋር በትብብር እንድትስራ ማድረጋቸውም በመካከለኛው ምስራቅ ብሎም በአለማቀፋዊ መድረኮች ድምጿ በጉልህ እንዲሰማ አድርጓል።
ፈጥኖ ደራሽነት
ኤምሬትስ በሼክ ካሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን የስልጣን ዘመን በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ፈጥና ደርሳለች።
ሰላምና መረጋጋት በጠፋባቸው ሀገራት ሰላማዊ አማራጮችን ከመደገፍ ባለፈ በረሃብ ለሚሰቃዩ ህዝቦች የነፍስ አድን ምግብና ቁሳቁሶችን በመላክ አጋርነትን በገሃድ ማሳየት ችላለች።
ከፈረንጆቹ 1972 ጀምሮ ባቋቋመችው የውጭ እርዳታ ማዕከሏ በኩል ተጠቃሚ የሆኑ ሀገራት ቁጥር 201 ደርሷል። እስከ 2021 አጋማሽ ድረስም 320 ቢሊየን ድርሃም ድጋፍ ማድረጓን መረጃዎች ያሳያሉ።