ምርጫ ቦርድ ለህወሓት ህጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያሰችል የህግ አግባብ የለም አለ
ቦርዱ እንዳስታወቀው አሁን ላይ ግጭቱ በስምምነት በመፈታቱ ውሳኔው እንዲሽር ህወሓት መጠየቁን ገልጿል
ቦርዱ ህወሓት ህጋዊ ሰውነት የሚያገኘው በድጋሚ ለመመዝገብ ጥያቄ ሲያቀርብ እና ቦርዱ ሲፈቅድ ነው ብሏል
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ ለህወሓት ህጋዊ ሰውነት ለመመለስ የሚያስችል የህግ አሰራር የለም ብሏል።
ቦርዱ ህወሓትን ከህጋዊ የፖለቲካ ፖርቲነት የሰረዘው "ኃይልን መሰረት ባደረገ የአመጽ ተግባር ላይ ተሳትፏል" በሚል ምክንያት ነበር።
ቦርዱ ፖርቲው ከህጋዊ ፖርቲነት እንዲሰረዝ እና የፖርቲው ኃላፊዎችም በፖርቲው ስም እንዳይንቀሳቀሱ የሚል ውሳኔ አሳልፎ ነበር።
ትግራይ ክልልን ሲመራ የነበረው ህወሓት ከፌደራል መንግስት ጋር ያለው አለመግባባት ወደ ጦርነት ማምራቱን ተከትሎ ነበር ምርጫ ቦርድ ይህን ውሴኔ ያሳለፈው።
በህወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል ለሁለት አመታት የተካሄደው ጦርነት በፕሪቶሪያ የዘላቂ ተኩስ አቁም ስምምነት ሊቆም ችሏል።
ቦርዱ እንዳስታወቀው አሁን ላይ ግጭቱ በስምምነት በመፈታቱ ውሳኔው እንዲሽር ህወሓት መጠየቁን ገልጿል።
"ለቦርዱ ውሳኔ ምክንያት የሆነው ኃይልን መሰረት ያደረገ የአመጽ ተግባር አሁን ባይኖርም እንደገና ህጋዊ ሰውነቱን ለፖርቲው ለመመለስ የሚያችሉ ድንጋጌዎች በአዋጅ 1662/2011 ተደንግጎ አይገኝም" ብሏል ቦርዱ።
ምርጫ ቦርድ በዚህ ምክንያት ህወሓት ያቀረበውን የህጋዊ ሰውነት ይመለስልኝ ጥያቄ እንደማይቀበለው ገልጿል።
ህወሓት ህጋዊ ሰውነት የሚያገኘው በድጋሚ ለመመዝገብ ጥያቄ ሲያቀርብ እና ቦርዱ ሲፈቅድ ነው ብሏል።