ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን ማን ነበሩ ?
ፕሬዝዳንቱ የሼክ ዛይድ መጀመሪያ ልጅ ናቸው
ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን በ1948 በአል ዐይን ከተማ ነው የተወለዱት
አቡዳቢን ለረጅም ዓመታት በመምራት የሚታወቁት ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን የተወለዱት እ.አ.አ በ 1948 መሆኑን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡
በአል ዐይን ከተማ በሚገኘው አል ሙዋጅ ቤተ መንግስት የተወለዱት ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን የሼክ ዛይድ የመጀመሪያ ልጅ ናቸው።
ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን ትምህርታቸውን የተከታተሉት በአባታቸው ሼክ ዛይድ በተመሰረተውና በትውልድ ከተማቸው በሚገኘው አል ናህያን ትምህርት ቤት ነው።
ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 1966 በምስራቅ የሀገሪቱ ግዛት፤ የአቡዳቢ ገዥ ተወካይና የሕግ ስርዓት ሃላፊ በመሆን መሾማቸው ይታወሳል።
ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን በ1969 የአቡዳቢ አልጋወራሽ መሆናቸው የሚታወስ ሲሆን፤ በ 1974 ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።
ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ፕሬዝዳንቱ እ.አ.አ በ 1976 የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ጦር ኃይሎች ምክትል አዛዥ ሆነው ማገልገላቸው ይታወሳል።
አባታቸው ሼክ ዛይድ በወቅቱ የአል ዐይን ግዛት ገዥ ስለነበሩ ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያንም ብዙውን ጊዜያቸውን ያሳለፉት ከአባታቸው ጋር እንደነበር የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን፤ አባታቸው ብዙ ስራዎችን ሲያከናውኑ አብረው ይከታተሉና ይንቀሳቀሱ እንደነበር ይገለጻል።
አባታቸው ሼክ ቢንዛይድም ቢሆኑ ብዙ ስራዎቻቸውን የሚያከናውኑት ከመጀመሪያ ልጃቸው ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን ጋር እንደነበር በርካቶች ይገልጻሉ።
ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን ለአባታቸው ታማኝ ከመሆናቸውም በላይ የሕዝብ ምክር ቤት ስብሰባዎች ላይም ይሳተፉ እንደነበር ተገልጿል።
ዛሬ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ሼክ ኸሊፋ ቢን ዛይድ አል ናህያን የመሪነትን ጥበብ የተማሩት ከአባታቸው እንደሆነም ይገራል። ሼክ ኸሊፋ ከአውሮፓውያኑ 2004 ጀምሮ ሀገራቸውን በፕሬዝዳንትነት በማገልገል ላይ ነበሩ።
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የፕሬዝዳንቱን ሞት ተከትሎ አንድ ወር ከ 10 ቀን ለሚሆን ጊዜ የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል ተብሏል።