የኢራኑ ካሚኒ የእስራኤል መሪዎች የሞት ፍርድ እንዲጣልባቸው ጠየቁ
የኢራኑ ጠቅላይ መሪ ካሚኒ አይሲሲ በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እና በቀድሞው መከላከያ ሚኒስትር ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ በቂ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል
አይሲሲ በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚኒን ኔታንያሁ፣በቀድሞው መከላከያ ሚኒስትር ዮአብ ጋላንት የእስር ማዘዣ አውጥቶባቸዋል
የኢራኑ ካሚኒ የእስራኤል መሪዎች የሞት ፍርድ እንዲጣልባቸው ጠይቀዋል።
የሀማስ እና ሄዝቦላ ታጣቂዎችን የምትደግፈው ኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ካሚኒ በእስራኤል የእስር ማዘዣ ማውጣት ሳይሆን የሞት ፍርድ ሊጣልባቸው እንደሚገባ መናገራቸውን በሮይተርስ ዘግቧል።
ካሚኒ አለምአቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት(አይሲሲ) ባለፈው ሀሙስ እለት በእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚኒን ኔታንያሁ፣በቀድሞው መከላከያ ሚኒስትር ዮአብ ጋላንት እና በሀማስ መሪ ኢብራሂም አል ማስሪ ላይ የእስር ማዘዣ እንዲወጣባቸው ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ አስተያየት ሰጥተዋል።
"የእስር ማዘዣ አውጥተዋል። ያ በቂ አይደለም። በእነዚህ ወንጀለኞች ላይ የእስር ማዘዣ መውጣት አለበት" ሲሉ ካሚኒ የእስራኤል ወታደሮችን በማመላከት ተናግረዋል።
የአይሲሲ ዳኞች በውሳኔያቸው ኔታንያሁ እና ዮአብ ጋላንት ግድያን፣ እስራትን እና ረሀብን አንደጦር መሳሪያነት ተጠቅመዋል ብሎ ለማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት አለ ብለዋል።
እስራኤል ውሳኔውን "አሳፋሪ" ስትል አውግዛዋለች። የጋዛ ነዋሪዎች ውሳኔ የሚደርስባቸውን ጥቃት እንደሚያስቆም እና ጥፋተኛ የሆኑት ተጠያቂ ይሆናሉ ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ እየጠየቁ ናቸው።
የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አጥብቃ የተቃወመችው እስራኤል በጋዛ የጦር ወንጀል አልፈጸምኩም ስትል አስተባብላለች።
የሀማስ መሪው ኢብራሂም አል ማርሲ የእስር ማዘዣ የወጣበት ለጦርነቱ መቀስቀስ ምክንያት በሆነው ባለፈው አመት ጥቅምት ወር እስራኤል ውስጥ በተፈጸመው የጅምላ ግድያ ወንጀል ተጠርጥሮ ነው። እስራኤል ባለፈው ሐምሌ ወር በፈጸመችው የአየር ጥቃት አል ማስሪ ወይም ማህመድ ዴይፍን መግደሏን ብትገልጽም፣ ሀማስ ግን አላረጋገጠም ወይም አላስተባበለም።
ባለፈው ጥቅምት 26 ኢራን በእስራኤል ላይ 200 ገደማ ሚሳይሎችን ካዘነበች ከሶስት ሳምንት በኋላ የእስራኤል ተዋጊ ጀቶች በኢራን ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ በሶስት ዙር ጥቃት ፈጽመዋል።
ኢራን እስራኤልን ለመበቀል በዝግጅት ላይ መሆኗን የካሚኒ አማካሪ በዛሬው እለት ተናግረዋል።