ሰዎች ኩላሊታችንን ግዙን እያሉ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እንደሚመጡ ተገለጸ
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ስር ለው ብሔራዊ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማዕከል በዓመት ለ100 ሰዎች የንቅለ ተከላ ህክምና የመስጠት አቅም ቢኖረኝም የግብዓት እጥረት አለብኝ ብሏል
በኢትዮጵያ የሰውነት አካልን መለገስ የሚፈቅድ ረቂቅ ህግ ከአንድ ወር በፊት ለፓርላማ መቅረቡ ይታወሳል
ሰዎች ኩላሊታችንን ግዙን እያሉ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል እንደሚመጡ ተገለጸ
ከመስከረም 2007 ጀምሮ ነበር በኢትዮጵያ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የተጀመረው፡፡ አዲስ አበባ በሚገኘው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ስር ሆኖ የጀመረው ይህ ብሔራዊ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ማዕከል አሁን ላይ ከኩላሊት፣ ጉበት እና ሌሎች የህክምና አይነቶች ጋር የተያያዙ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡
የማዕከሉ ዳይሬክተር ዶክተር ጸጋይ ብርሀነ ለአል ዐይን እንዳሉት ማዕከሉ ስራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በአጠቃላይ ለ187 ሰዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና አገልግሎት አድርጓል ብለዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት የሰዎችን አካላዊ ንኪኪ ለማስቀረት በሚል የንቅለ ተከላ ህክምናው ተቋርጦ እንደነበር የተናገሩት ዳይሬክተሩ ማዕከሉ ዳግም አገልግሎት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ደግሞ ለ24 ሰዎች የንቅለ ተከላ ህክምና መስጠቱን ተናግረዋል፡፡
ከኮቪድ በፊት ማዕከሉ በወር ለአራት ሰዎች የንቅለ ተከላ ህክምና ይሰራ ነበር የተባለ ሲሆን ወረርሽኙ መከሰቱን ተከትሎ በዲያሊሲ እና ወረፋ በመጠበቅ ላይ ከነበሩት ውስጥ አብዛኞቹ ህይወታቸው አልፎ እንደተገኘ ተገልጿል፡፡ ቶሎ ቶሎ ንቅለ ተከላውን በተሰራ ቁጥር የሟቾችን መጠን መቀነስ ይቻላልም ተብሏል፡፡
አሁን ላይ ማዕከሉ በሳምንት እስከ ሶስት በዓመት ደግሞ እስከ 100 ሰዎች ድረስ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና የመስጠት አቅም እንዳለው የሚናገሩት ዶክተር ጸጋይ በግብዓት እጥረት ምክንያት በአቅሙ ልክ እየሰራ እንዳልሆነም ገልጸዋል፡፡
“ማዕከሉ አሁን ላይ የንቅለ ተከላ ህክምና አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል የሰው ሀይል ችግር ባይኖርበትም የአይሲው፣ አልጋ፣ መድሃኒቶች፣ የቤተ ሙከራ ግብዓቶች እና ሌሎች ምርቶች እጥረት አለበት” ሲሉም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡
በግብዓት እጥረቱ ምክንያትም ህክምናውን የሚፈልጉ ዜጎች እና እየሰጠን ያለው የህክምና አገልግሎት እንዳይመጣጠን አድርጓል ያሉት ዳይሬክተሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህክምና ፈልገው የሚመጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ህክምናውን ፈልገው የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ለምን ሊጨምር ቻለ? በሚል ላቀረብንላቸው ጥያቄ “ይህ የሆነው የህብረተሰቡ ግንዛቤ እያደገ ስለመጣ፣ ንቅለ ተከላ ከተደረገ በኋላ ብዙዎቹ ውጤታማ ስለሆኑ እና ሰዎች ይህን ፈልገው ስለሚመጡ፣ የታማሚዎች ቁጥር በተለያዩ ምክንያቶች እየጨመረ ስለመጣ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ” ብለዋል፡፡
ማዕከሉ አሁን ላይ ከ500 በላይ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ላደረጉ ታካሚዎች የህክምና ክትትል በማድረግ ላይ መሆኑንም ሰምተናል፡፡
ከዚህ በፊት የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና እዚህ አናደርግም የሚሉ ሰዎች ነበሩ የሚሉት ዳይሬክተሩ ይህ አመለካከት ቀስ በቀስ እየቀነሰ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡
አሁን ባለው የህክምና ወጪ መሰረት አንድ ሰው ወደ ውጭ ሀገራት ሄዶ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ለማግኘት በአማካኝ 30 ሺህ ዶላር እንደሚያወጣ የተናገሩት ዶክተር ጸጋይ ህክምናውን በሀገር ውስጥ ሲያደርጉ ግን ይህን ወጪ ከግማሽ በላይ መቀነስ ይቻላልም ብለዋል፡፡
ህክምናውን ለማግኘት መስፈርቱ ምንድን ነው? የኩላሊት ንቅለ ተከላውን እንዴት ነው የምትፈጽሙት? ለሚሉት ጥያቄዎች “ወረፋው ነው፡፡ ቶሎ የሚጠበቅበትን ያሟላ ቶሎ ህክምናውን ያገኛል፡፡
የንቅለ ተከላ ፕሮቶኮል የሚባል መመሪያ አለ በዚህ መመሪያ መሰረትም የንቅለ ተከላ ቡድን የሚመለከታቸው የህክምና ቡድን አባላትን ጨምሮ የህግ፣ ስነ ልቦና እና ሶሻር ወርከርን ጨምሮ በጋራ አንድ ሰው ንቅለ ተከላ ህክምናውን ለማድረግ የተቀመጡ መስፈርቶችን አሟልቷል ወይ የሚለውን በሚገባ ከመረመርን በኋላ ለጤና ሚኒስቴር እንልካለን” ብለዋል ዶክተር ጸጋይ፡፡
ጤና ሚኒስቴር ደግሞ ከማዕከሉ የቀረበለትን የንቅለ ተከላ ፕሮቶኮል በብሔራዊ የንቅለ ተከላ ቦርድ አማካኝነት ንቅለ ተከላው እንዲደረግ የመጨረሻ ውሳኔ ሲሰጥ ህክምናው ለታካሚዎች እንደሚሰጥ ዶክተር ጸጋይ አክለዋል፡፡
አሁን ላይ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምናን ለማግኘት የኩላሊት ልገሳ የስጋ ዝምድና ባላቸው ወይም ከባል አልያም ከሚስት ከሚገኝ ልገሳ ብቻ እንደሚካሄድም ሰምተናል፡፡
ታካሚዎች ኩላሊት በልገሳ የሚያገኙበት አማራጭ አልጠበበም? በሚል ለዶክተር ጸጋይ ላቀረብነው ጥያቄ እውነት ነው በብዙ ስጋቶች ምክንያት አሁን ላይ ታማሚዎች የስጋ ዝምድና ካላቸው አልያም ከባል/ሚስት ብቻ በሚገኝ ልገሳ ህክምናውን እንዲያገኙ የሚስገድድ አሰራር አለ፣ ይህ መሆኑ ልገሳውን አጥብቦታል፡፡ የትዳር አጋር፣ የስጋ ዘመድ ወይም የሚገጥም ኩላሊት ያለው ሰው ማገኘት አስቸጋሪ የሚሆንባቸው ሰዎች ያጋጥማል ብለዋል፡፡
የኩላሊት ልገሳ የሚደረግባቸውን አማራጮች ማስፋት አይቻልም፣ እርስዎ እንደባለሙያ ምን ይመክራሉ? ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄም በርካታ ሀገራት መሰል ችግሮችን ለመፍታት ብዙ አማራጮችን ይከተላሉ እኛም ሀገር ህጉ ትንሽ ሰፋ ቢል የተሻለ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የአካል ልገሳ ጉዳይ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ ጉዳይ ነው የሚሉት ዶክተር ጸጋይ ኩላሊታችንን መሸጥ እንፈልጋለን፣ ኩላሊታችንን ግዙን የሚሉ ዜጎች ወደ ማዕከሉ እንደሚመጡም አክለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሰውነት አካልን መለገስ የሚፈቅድ ረቂቅ ህግ ከአንድ ወር በፊት ለፓርላማ መቅረቡ ይታወሳል፡፡
በዚህ ረቂ ህግ መሰረት ማንኛውም ሰው አግባብነት ባለው አካል ፊት ቀርቦ በሚሰጠው ፈቃድ መሰረት ደም፣ ህዋሱን፣ ህብረ ህዋሱን፣ የአካል ክፍሉን፣ አካሉን መለገስ እንደሚችል ይፈቅዳል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የህዋስ፣ የሕብረ - ህዋስ፣ የአካል ክፍል እና የአካል ንቅለ ተከላ ህክምናን ማከናዎን የሚቻለው የተቀባዩን ህይወት ለማቆየት ወይም የሰውነት አቋሙን ለማስተካከል ሌላ የተሻለ አማራጭ መንገድ የማይገኝ መሆኑ በህክምና ቦርድ ሲረጋገጥ ብቻ እንደሆነ ረቂቁ ይደነግጋል፡፡
ይሁንና ማንኛውም ሰው በሽያጭ ወይም ሌላ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት ሲባል ደም፣ ህዋስ፣ ህብረ ህዋስን፤ የአካል ክፍል እና አካልን መለገስም ሆነ መቀበል የተከለከለ ሲሆን ከህጋዊ የልገሳ ስርዓት ውጭ የተገኘ አካል፤ የአካል ክፍል፤ ሕብረ ሕዋስ ወይም ሕዋስ አገልግሎት ላይ ማዋልንም ይከለክላል፡፡
እንዲሁም ማንኛውም ሰው ህይወቱ ሲያልፍ ህዋሱን፣ህብረ ህዋሱን ፤ የአካል ክፍሉን ወይም አካሉን ለመለገስ ፈቃዱን አግባብነት ላለው አካል እንዲለግስ ሲፈቅድ ነገር ግን ለጋሹ ሕዋሱን፣ ሕብረ ሕዋሱን፣ የአካል ክፍሉን ወይም አካሉን የሚቀበለውን ሰው መምረጥ እንዳይችል በረቂቅ ህጉ ላይ ሰፍሯል፡፡
በሕግ ከለላ ስር ከሚገኝ ሰው የአካል ክፍል ወይም አካል መውሰድ የሚቻለው ተቀባዩ የቅርብ ዘመድ ሲሆን ብቻ ነው የተባለ ሲሆን የለጋሹ አካል ክፍል ለተቀባይ ተስማሚ በማይሆንበት ጊዜ የሚስማማ አካል ካለው ከሌላ ለጋሽ ጋር መለዋወጥን ፈቅዳል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ከእንስሳት ወይም ከባዮቴክኖሎጂ የተገኙ ውጤቶችን ለንቅለ ተከላ ሕክምና አገልግሎት እንዲውሉ ሊፈቀድ እንደሚችል ይህ ረቂቅ አዋጅ ይደነግጋል፡፡
የኩላሊት ህመምተኞች እጥበት በጎ አድራጎት ድርጅት ስራ አስኪጅ አቶ ሰለሞን አሰፋ በበኩላቸው የኩላሊት ህክምና የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ ቢሆንም ተገቢው ትኩረት አልተሰጠውም ብለዋል፡፡
የኩላሊት ንቅለ ተከላ ህክምና ማዕከል አንድ ብቻ መሆኑ፣ የአካል ልገሳ ለማድረግ ያለው አሰራር እጅግ ጠባብ መሆኑ፣ የዲያሊሲስ ዋጋ በየጊዜው እየጨመረያ በመሆኑ ለራሳቸው እና ለሀገራቸው መስራት የሚችሉ ዜጎች በቀላሉ ህይወታቸው እንዲያልፍ እያደረገ መሆኑንም ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡