ዩክሬን፤ ሩሲያ ለዩክሬናውያን የተፋጠነ ዜግነት መስጠት መጀመሯን አወገዘች
ሩሲያ ለደቡባዊ ዩክሬን ነዋሪዎች ዜግነት ለመስጠት የሚያስችል አዲስ አዋጅ ይፋ ማድረጓ ይታወሳል
አሜሪካም ዩክሬናውያንን በግድ ለማስገበር ነው በሚል እርምጃውን አውግዛለች
ዩክሬን፤ ሩሲያ ለዩክሬናውያን ዜግነት መስጠት መጀመሯን አወገዘች፡፡
የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "በዩክሬን ሉዓላዊነትና ግዛታዊ አንድነት ላይ የተቃጣ ሌላኛው ጥሰት" ሲል የሩሲያን ድርጊት በጽኑ አውግዟል፡፡
የሩሲው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬናውያን የሩሲያን ዜግነት ሊያገኙ የሚችሉባቸውን መንገዶች የሚያቀል አዲስ አዋጅ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
አዋጁ በሩሲያ ጦር እና በደጋፊዎቹ ቁጥጥር ስር በዋሉ የዩክሬን ግዛቶች ለሚገኙ ዜጎች የተፋጠነ ፓስፖርት አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል ነው፡፡
ፑቲን የፈረሙት አዲሱ አዋጅ አዲሱ አዋጅ በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኙት የዛፖሪዢያ እና ኬርሰን አካባቢ ነዋሪዎች የሩሲያ ፓስፖርት እንዲያገኙ ለማድረግ ያስችላል መባሉን ነው ኤ.ኤፍ.ፒ የዘገበው፡፡
ሆኖም እርምጃውን የተቃወሙ የኪቭ ባለስልጣናት አዋጁ ህጋዊነት እንደሌለውና ተቀባይነት እንደማያገኝ አሳስበዋል፡፡
እርምጃው የዩክሬንን ሉዓላዊነትና ግዛታዊ አንድነት የሚጥስ ዓለም አቀፍ ህግጋትን የሚጥስ እንደሆነም ነው ባለስልጣናቱ የገለጹት፡፡
አሜሪካም የሩሲያን ድርጊት አውግዛለች፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ሩሲያ ዩክሬናውያንን በግድ ለማስገበር እየሞከረች ነው በሚል አጥብቀን የምንቃወመው ነው ሲሉ እርምጃውን አውግዘዋል፡፡
ሩሲያ ልዩ ያለችውን ዘመቻ ባሳለፍነው የካቲት ወር ከጀመረች 5 ገደማ ወራት ተቆጥረዋል፡፡