በውጭ ያለው የሩሲያ ባለሃብቶች ሃብት ተወርሶ ለመልሶ ግንባታው እንዲውል ጠይቃለች
ዩክሬን በሶስት ምዕራፎች ለማከናወን ላሰበችው የመልሶ ግንባታ እቅድ 750 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት ገለጸች፡፡
በዩክሬን መልሶ ግንባታ ላይ ያተኮረ ጉባዔ በስዊዘርላንድ ተካሂዷል፡፡
በኮንፈረንሱ የተገኙት የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ዴኒስ ሽሚጋል ሃገራቸው በጦርነቱ ምክንያት ከ100 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የመሰረተ ልማት ውድመት እንደረሰባት ተናግረዋል፡፡
ውድመቱ ከዚህም በላይ መክፋቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ 750 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ የሚገመተውን የመልሶ ግንባታ ወጪ ማን ይሸፍን? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
መንግስታቸው በተለያዩ ሀገራት ያለው የሩሲያ "ኦሊጋርኮች" ሃብት ተወርሶ ለመልሶ ግንባታው መዋል አለበት የሚል ውጥን እንዳለውም አስታውቀዋል፡፡
የመልሶ ግንባታ እቅዱ በሶስት የተለያዩ ምዕራፎች ተከፋፍሎ የሚፈጸም ነው እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፡፡
መሰረታዊ ለሚባሉ የምግብና የጤና፣ የውሃ እና ሌሎችም መሰረት ልማቶች ቀድሚያ ተሰጥቶ ሃገሪቱን በቶሎ መልሶ ለመገንባት ጥረት እንደሚደረግም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
የሩሲያን ድርጊት በመቃወም የተለያዩ እገዳዎችን የጣሉ የምዕራብ ሃገራት ከፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር የቀረበ ግንኙነት አላቸው ባሏቸው የሩሲያ ቱጃሮች ላይ እገዳዎችን መጣላቸው ይታወሳል፡፡