የሩሲያ ጦር በክልሉ የመጨረሻ ዩክሬን ይዞታ የነበረችውን ሊስቻንስክን ተቆጣጥረዋል
የሩሲያ ጦር እና በሩሲያ የሚደገፉ ኃይሎች በዩክሬን የሚገኘውን የዶንባ ክልልን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒሰትር ሰርጌ ሾይጉ፤ “ወታደሮቻችን በሉሀንስክ ህዝቦች ሪፐብሊክ ውስጥ የቀሩ የዩክሬን ኃይሎችን ሙሉ በሙሉ ጠራርገው አስወጥተዋል” ማለታቸውን የሩሲያው አር ቲ ዘግቧል።
የሩሲያ ጦር እና የዶንባስ ኃይሎች በክልሉ የሚገኝ የመጨረሻዋን ወሳኝ ከተማ የሆነችውን ሊስቻንስክ ከተማ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ባገባደድነው ሳምንት በሊስቻንስክ ከተማ ከባድ ውጊያ ውስጥ እንደነበሩ ይታወሳል።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ዶናባስ ክልል ሙሉ በሙሉ በሩሲያ እጅ መውደቁ ለሩሲያ ትልቅ ስኬት መሆኑ እየተነገረ ነው።
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነትነት ከማቅናቷ ከቀናት በፊት ለዶንባስ ክልል የሀገርነት እውቅና መስጠቷ አይዘነጋም።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ነበር ከሩሲያ ጋር ወደለየለት ጦርነት ያመሩት።
ሁለቱ ሀገራት ጦርነት ከጀመሩ 130 ቀኑ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከ15 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል።