የሩሲያ ጦር በምዕራብ ዩክሬን በኩል አዲስ ጥቃት መክፈቷ ተገልጿል
ሊሲቻንስክ ከተማ በሩሲያ ጦር መያዟን ዩክሬን አስታወቀች፡፡
የሩሲያ ጦር ሊሲቻንስክ ጨምሮ ዶንባስ ክልልን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን ከቀናት በፊት መናገሩ ይታወሳል፡፡
የዩክሬን መከላከያ ዛሬ እንዳሳወቀው የሩሲያ ጦር በክልሉ የመጨረሻ ዩክሬን ይዞታ የነበረችውን ሊስቻንስክን ተቆጣጥሯል ብሏል፡፡
የዩክሬን ወታደሮች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ መደረጉ ትክክለኛ ውሳኔ ነው ያለው የዩክሬን መከላከያ በቀጣይ በሩሲያ ጦር ስር የገቡ ቦታዎችን ሙሉ ለሙሉ ማስለቀቅ የሚያስችሉ ዘመቻዎችን እንጀምራለን ሲልም አስታውቋል፡፡
የሩሲያ ጦር እና በሩሲያ የሚደገፉ ኃይሎች በዩክሬን የሚገኘውን የዶንባስ ክልልን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሩሲያ ጦር በርካታ ጥሩ እድሎች በእጁ አሉ ያለው የዩክሬን መከላከያ መግለጫ በጦር መሳሪያ፣በተዋጊዎች ብዛት እና በሌሎች ድጋፎች ከዩክሬን የተሻሉ ናቸውም ብሏል፡፡
ይህ ሁሉ ባለበት የዩክሬን ተዋጊዎችን ከሩሲያ ጋር የጀመራችሁትን ጦርነት ቀጥሉበት ማለት በዜጎች ህይወት መቀለድ በመሆኑ ጦራችን ሊሲቻንስክ ከተማን ለቆ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ አድርገናል ሲል ተቋሙ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡
የሩሲያ መከላከያ ሚኒሰትር ሰርጌ ሾይጉ፤ “ወታደሮቻችን በሉሀንስክ ህዝቦች ሪፐብሊክ ውስጥ የቀሩ የዩክሬን ኃይሎችን ሙሉ በሙሉ ጠራርገው አስወጥተዋል” ማለታቸውን የሩሲያው አር ቲ ዘግቧል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለሚያደርጉልን ሀገራት ምስጋና ይግባና በሩሲያ ጦር የተያዙ አካባቢዎችን መልሰን እንቆጣጠራለን ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የሩሲያዋ ቺቺኒያ ግዛት ሪፐብሊክ መሪ ራምዛን ከዲሮቭ የሊሲቻንስክ ከተማን ሲቆጣጠሩ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ሚዲያዎች አጋርተዋል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለም የሩሲያ ጦር በምዕራብ ዩክሬን በኩል የስሎቭያንስክ ከተማን ለመቆጣጠር ከባድ ውጊያ መጀመሩ ተገልጿል፡፡