ዩክሬን የሩሲያን ስም ወደ ''ሞስኮቪያ'' ለመቀየር እያጤንኩ ነው አለች
ሩሲያ በበኩሏ የዩክሬን መጠሪያ ወደ "ስቼዊኒስች" እንዲቀየር ምክረ ሀሳብ አቅርባለች
"ስቼዊኒስች" በጀርመንኛ ስግብግብ የሚል ትርጓሜ አለው
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪ መንግስታቸው ለሩሲያ አዲስ ስያሜ እንዲያወጣ ማዘዛቸው ተነግሯል።
አዲሱ የሩሲያ ስም “ሞስኮቪያ” እንዲሆን ሃሳባቸውን ማቅረባቸውም ነው የተገለጸው።
“ሩሲያ” የሚለው ስም ዩክሬናውያን የዘር ግንዳችን መነሻ ነው ከሚሉት “ኬይቫን ሩስ” ወይም “ሩስ” የተወሰደ በመሆኑ መለወጥ አለበት የሚለው ሃሳብ በዩክሬናውያን ብሄርተኞች ተደጋግሞ ይነሳል።
“ኬይቫን ሩስ” ከ8ኛው እስከ 13ኛው ክፍለዘመን ትልቅ ሀገር የነበረና ወደተለያዩ ሀገራት የተከፋፈለ መሆኑንም በመጥቀስ፥ “ሩሲያ” የሚለው ስያሜ የቭላድሚር ፑቲን ሀገርን “የመስፋፋት” ፍላጎት ሳይጨምረው እንዳልቀረ እምነታቸውን ይገልጻሉ።
- በባክሙት በተደረገ ጦርነት በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች መገደላቸው ተገለጸ
- የሩሲያው ፓትሪያርክ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ባላት ቤተክርስቲያን ላይ የምትፈጥረውን ተጽእኖ እንድታቆም ጠየቁ
አዲሱ ዩክሬን ለሩሲያ ያወጣችው መጠሪያ ስም “ሞስኮቪያ” ግን የ“ኬይቫን ሩስ” አንድ ግዛት የነበረች በመሆኑ “የሩሲያን የግዛት ማስፋፋት ፍላጎት” እንደሚገድብ ነው የዜለንስኪ አስተዳደር ያመነው።
አዲሱን ስም ለማውጣት ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች ፊርማ መሰብሰቡ የተነገረ ሲሆን፥ የዩክሬኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴኒስ ሽሚጋል ሂደቱን እየመሩ ይገኛሉ ብሏል የሩሲያን ታይምስ ዘገባ።
ዜለንስኪ የስም ለውጡ የታሪክ እና ባህል መሰረት የያዘና ከአለም አቀፍ ህግ ጋር የማይጻረር እንዲሆን ማዘዛቸውም ተገልጿል።
ዩክሬን ባለፉት አመታትም ከሩሲያ ወይንም ከቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ጋር ትስስር ያላቸው የሚመስሉ የከተሞች ስሞችን የቀየረች ሲሆን፥ ከባለፈው አመት ጦርነት ወዲህም ይሄው ስያሜን የመቀየር ፍላጎት ጎልቶ መውጣቱ ይነገራል።
ዩክሬን “ለሩሲያ አዲስ ስም ለማውጣት እያጤንኩ ነው” ማለቷን ተከትሎም ክሬምሊን ምላሽ ሰጥቷል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫ “ዩክሬን ለሩሲያ አዲስ ስም አወጣለሁ ማለቷ በዩክሬን ምድር ሩሲያ ጠል ትውልድ የመፍጠር ጥረቷ አንዷ ማሳያ ነው” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪን “የዩክሬኑ ናዚ” የሚል ስም የሰጧቸው የሩሲያ የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭም ፥ ለዩክሬን "ስቼዊኒስች ባንዴራ ሬች” የሚል ስም አውጥተዋል።
ስያሜው ጀርመን ሶቪየት ህብረትን ስትወር የአዶልፍ ሂትለር ተባባሪ ነው ከምትለው ዩክሬናዊው ስቴፈን ባንዴራ ጋር የተያያዘና ከፊት ያስቀመጡት “ስቼዊኒስች” የሚለው ቃልም በጀርመንኛ “ስግብግብ” የሚል ትርጉም ያለው ነው ተብሏል።
ከአንድ አመት በላይ ጦርነት ውስጥ ያሉት ሁለቱ ሀገራት አሁን ደግሞ በስም ለውጥ ዙሪያ የቃላት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል።