ሩሲያ ወደ ዩክሬን 81 ሚሳኤሎችን መተኮሷ ተገለጸ
ከተወነጨፉት ሚሳኤሎች ውስጥ 34ቱን መትታ መጣሏን ያሳወቀችው ኬቭ፥ አራት ኢራን ሰራሽ ድሮኖችንም መትቻለሁ ብላለች
ሩሲያ በበኩሏ የዛፓሮዥያ የኒዩክሌር ጣቢያ ሃይል ከዋናው መስመር እንዲለያይ የተደረገው ጸብ ለመጫር ነው በሚል ክሱን አጣጥላለች
ሩሲያ በዩክሬን የተለያዩ ከተሞች ከጥር ወር ወዲህ ከፍተኛውን የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሟ ተነገረ።
ኬርሰን፣ ሌቪቭ፣ ኦዴሳ፣ ክራኬቭ እና ዛይቶር የተሰኙት ከተሞች ላይ የወደቁት ሚሳኤሎች በጥቂቱ የዘጠኝ ሰዎችን ህይወት መቅጠፋቸውን የዩክሬን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የዩክሬን ጦር በዛሬው እለት ብቻ ሩሲያ 81 ሚሳኤሎችን መተኮሷን ገልጾ፥ ከዚህ ውስጥ 34ቱን መትቼ ጥያለሁ ብሏል።
በጦሩ ተመተው ከወደቁት ውስጥ አራት ኢራን ሰራሽ ድሮኖችም እንደሚገኙበት ጦሩ ይፋ አድርጓል።
በርካታ ህንጻዎችን ያፈራረሱት ጥቃቶች የሃይል መቋረጥ ማስከተላቸው ነው የተገለጸው።
መዲናዋ ኬቭም የሚሳኤል ጥቃት ደርሶባታል የተባለ ሲሆን፥ የደረሰው ጉዳት ግን በቢቢሲ ዘገባ ላይ አልሰፈረም።
ከ10 የኬቭ ነዋሪዎች አሁን ላይ ኤሌትሪክ የሚጋያገኘው አራቱ ብቻ ነው ብለዋል የከተማዋ ከንቲባ ቪታሊ ክሊትሽኮ።
ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪም የተቋረጡ የኤሌክትሪክ አገልግሎቶችን ዳግም ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው ማለታቸ ተጠቅሷል።
በሚሳኤል ጥቃቶቹ ምክንያት የዛፓሮዥያ የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ ጣቢያን ከዩክሬን የሃይል ስርአት ጋር የሚያገናኘው መስመር በመመታቱ በርካታ ከተሞች ጨለማ ውስጥ ናቸው ብሏል አሾሼትድ ፕረስ በዘገባው።
በሩሲያ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የኒዩክሌር ሃይል ማመንጫ በተደጋጋሚ በደረሰበት ጥቃት ምክንያት አሁን ላይ በናፍጣ በሚሰሩ ጀነሬተሮች ብቻ ኤሌክትሪክ እያመነጨ ይገኛል፤ በዛሬው እለት በተፈጸሙ ጥቃቶች ግን ሃይል ማስተላለፉን አቋርጧል።
ሞስኮ በዛፓሮዥያ የመሰረተችው አስተዳደር ግን የኬቭን ክስ አይቀበለውም።
በዩክሬን ቁጥጥር ስር ከሚገኘው የዛፓሮዥያ ክፍል መቅረብ የነበረባቸው የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግብአቶች (ነዳጅ) አለመቅረባቸውን በመጥቀስ ግንኙነቱን ያቋረጠችው ኬቭ ግልጽ ጸብ አጫሪ ድርጊት ፈጽማለች ብሏል።
የሞስኮ ባለስልጣናት ግን በሚሳኤል ጥቃቶቹ ዙሪያ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።