የሩሲያው ፓትሪያርክ ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ባላት ቤተክርስቲያን ላይ የምትፈጥረውን ተጽእኖ እንድታቆም ጠየቁ
የኬቭ መንግስት የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከተመሰረተችበት ገዳም ለቃ እንድትወጣ ማዘዙ ይታወሳል
የሩሲያው ፓትሪርክ "የዩክሬናውያን ምዕመናን መብት እና ነጻነት በገሃድ እየተጣሰ ነው" ብለዋል
የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ኪሪል ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ባላት ቤተክርስቲያን ላይ የምትፈጥረውን ተጽእኖ እንድታቆም ጠየቁ፡፡
የኬቭ መንግስት የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከተመሰረተችበትና ረዥም ዘመናት ካስቆጠረው ገዳም ለቃ እንድትወጣ ያዘዘው አርብ እለት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ዩክሬን ውሳኔውን ያሳለፈችው ቤተክርስቲያኗ ከሞስኮ ጋር ትተባበራለች እንዲሁም የክሬምሊን ባለስልጣናት ደጋፊ ናት በሚል ነው፡፡
በዚህም ከጥቅምት ወር ጀምሮ የዩክሬን የደህንነት አገልግሎት በዩክሬን አብያተ ክርስቲያናት ላይ በየጊዜው ፍተሻ ሲያደርግ መቆየቱ፣ በጳጳሳቱ እና የገንዘብ ድጋፍ በሚያደርጉ ላይ ማዕቀብ መጣሉ እንዲሁም በደርዘን በሚቆጠሩ ቀሳውስት ላይ የወንጀል ክስ መክፈቱን ነው ሬውተርስ የዘገበው።
የዩክሬን ባህል ሚኒስቴር ፤ የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እስከ መጋቢት 29 ባለው ጊዜ ውስጥ 980 አመታት ካስቆጠረው የኪቭ-ፔቸርስክ ላቭራ ገዳም ግቢ መልቀቅ አለባት ሲል አሳስቧል፡፡
የሩሲያው ፓትሪያርክ የዩክሬን መንግስት ውሳኔን ተቃውሞውታል፡፡
ኪሪል የዩክሬን ምዕመናን መብት እና ነጻነት በገሃድ እየተጣሰ መሆኑ የሚያሳዝን ነው ብለዋል።
ፓትሪያርኩ የተወሰደሰውን እርምጃ በመቃውም የካቶሊኩ አባ ፍራንሲስን እና ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ዩክሬን ከድርጊቷ እንድትቆጠብ እንዲያሳምኑ ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
“ገዳሙን በኃይል መዝጋት በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዩክሬን አማኞች መብት መጣስ ነው” ያሉት ፓትሪያርኩ፤ የሃይማኖት መሪዎች እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ድርጊቱን ለማስቆም የተቻላቸውን እንዲደርጉ ማሳሰባቸውም በቤተክርስቲያኗ ድረ ገፅ ላይ የወጣው መግለጫ አትቷል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ እያካሄደቸው ያለውን ወታደራዊ ዘመቻ ይደግፋሉ በሚል የሚወቀሱት ፓትሪያርክ ኪሪል ይህን ይበሉ እንጅ፤ የዩክሬን ቤተክርስቲያን የተለየ አቋም እንዳላት ስታሳውቅ ቆይታለች፡፡
ቤተክርስቲያኗ ከሞስኮ ፓትርያርክ ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋርጫለሁ ማለቷም አይዘነጋም፡፡