የሰሜን ኮሪያው መሪ የጠላትን ጥቃት ለመከላከል ሁሌም ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል አሉ
ሰሜን ኮሪያ፤ በደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ አየር ማረፊያ ላይ ያነጣጠረ የሚመስል ወታደራዊ ልምምድ እያከሄደች ነው
ኪም “የኪም ወራሽ” ልትሆን እንደምትችል እየተነገረላት ካለው ሴት ልጃቸው ጋር መታየታቸው አሁንም አነጋጋሪ ሆኗል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የጠላትን ጥቃት ለመከላከል ሁሌም ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል አሉ፡
ኪም ይህን ያሉት በምዕራባዊ ግንባር የሚገኘውን የሃዋሶንግ የመድፍ አሃድ “በደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ አየር ማረፊያ ላይ ያነጣጠረ የሚመስል” ወታደራዊ ልምምድ ሲያደርግ በተመለከቱበትና የአሃዱን ወቅታዊ አቅም በገመገሙበት በዛሬው እለት ነው፡፡
ኪም “በጦርነት መከላከል” ወቅት “ለሁሉም ድፍረት የተሞላበት እንቅስቃሴ ንቁ መሆን እንዲሁም በጠላት ለሚደረገው ማንኛውንም የጦርነት ዝግጅት በከፍተኛ ሁኔታ ምላሽ መስጠት” እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ሲል የሰሜን ኮሪያው ሴንትራ.ል ኒውስ ኤጅንሲ ዘግቧል።
ሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ልምምዱን ያካሄደችው ደቡብ ኮሪያ በትናንትናው እለት ፒዮንጊያን የረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳይል ወደ ቢጫው ባህር አስወንጭፋለች የሚል ክስ ማቅረቧን ተከትሎ መሆኑ ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኪም ወታደራዊ ልምምዱን የተመለከቱት ከሴት ልጃቸው ጋር መሆኑ አነጋጋሪ አጀንዳ መሆኑ አልቀረም፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከአባቷ ጋር በመሰል ወታደራዊ ትእይንቶችና ዝግጅቶች ላይ በመገኘት በቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ማለት የጀመረችው የፕሬዝዳንቱ ሴት ልጅ፤ አሁን ላይ ጥቀር ኮት ለብሳ የመድፍ አሃዱን ልምምድ ስትመለከት የኮሪያ ሴንትራል ኒውስ ኤጀንሲ ያሰራጨው ምስል ያሳያል፡፡
ይህም ኪም ጁ ኤ በመባል የምትታወቀው የፕሬዝዳንቱ ሁለተኛ ሴት ልጅ ቀጣይዋ የሰሜን ኮሪያ መሪ ልትሆን ትችላለች የሚለውን ጥርጣሬ ከፍ ያደረገ መሆኑ በርካቶች ያነሳሉ፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኮሪያ ሴንትራል ቴሌቪዥንን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሚዲያዎች "ተወዳጅ" እና "የተከበረች" የመሳሰሉ ቅጽሎችን በማስቀደም የተለያዩ ዜናዎች የሚሰሩላትም ናት ኪም ጁ ኤ፡፡
“የኪም ወራሽ” የሚል ርዕስ ይዘው አስከ መውጣት የደረሱ መገናኛ ብዙሃንም በርካቶች ናቸው፡፡
በተጨማሪም የሰሜን ኮሪያ ፖስታ ቤት የፕሬዝዳንቱ ልጅ ምስል ያላቸው ቴምብሮች ይፋ ማድጉ አይዘነጋም፡፡