ሰሜን ኮሪያ በግብርና ዘርፍ 'መሰረታዊ ለውጥ' እንዲደረግ አዘዘች
ኪም ጆንግ ኡን መሰረታዊ ለውጥ እንዲደረግ ያሳሰቡት በሀገሪቱ የምግብ እጥረት እየጨመረ መምጣቱ በተዘገበበት ወቅት ነው
ሀገሪቱ ለውጡን ለማምጣት ምን አይነት እርምጃዎችን እንደምትወስድ ግን ያለችው ነገር የለም
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የመንግስት ባለስልጣናት በግብርናው ዘርፍ ላይ "መሰረታዊ ለውጥ" የሚያመጡ ስራዎችን እንዲከውኑ አሳስበዋል።
መሪው ይህን ያሉት የሀገሪቱ የምግብ እጥረት እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ ነው ተብሏል።
ኪም በዚህ ዓመት የምግብ እህል ምርታማነትን የማሳደግ ስራዎች ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው ትናንት በተካሄደው የፓርቲያቸው የማዕከላዊ ኮሚቴ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ መናገራቸውንም የሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥኝ ኬ ሲ ኤን ኤ ዘግቧል።
- ሰሜን ኮሪያ የዓለም ትልቁ የኒውክሌር ኃይል ባለቤት ትሆናለች - ኪም ጆንግ ኡን
- የጸጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኮሪያ የሚሳይል ሙከራ ዙሪያ “ዝምታን መምረጡ” አሳፋሪ ነው - አሜሪካ
የመንግስት የዜና ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ እንደዘገበው ሀገሪቱ ለውጡን ለማምጣት ምን አይነት እርምጃዎችን እንደምትወስድ አላብራራችም።
ኪም ግን ለውጡ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ መከሰት አለበት ብለዋል።
በሰሜን ኮሪያ ያጋጠመው የምግብ እጥረት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱ እየተዘገበ ነው።
ፒዮንግያንግ ግን ለዜጎቿ ምግብ ማቅረብ አትችልም የሚለውን ሀሳብ ውድቅ ማድረጓን ነው ሬውተርስ የዘገበው።
በትናንቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ኪም የሶሻሊስት ስርአት ግንባታን በማረጋገጥ ረገድ የግብርና እድገት ያለውን ጠቀሜታ ጠቅሰዋል።
ሰሜን ኮሪያ በኒውክሌር ጦር መሳሪያዎቿ እና በባለስቲክ ሚሳይል ፕሮግራሞቿ ላይ ጥብቅ ዓለም አቀፍ ማዕቀብ እየተጣለባት ነው።
ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘም ድንበሮቿን መዝጋቷም ምጣኔ ሃብታዊ ፈተናዋን አብዝቶታል ነው የተባለው።
በሰሜን ኮሪያ ያለውን የምግብ እጥረት ሁኔታ የሚያሳይ መረጃ ይፋ አልተደረገም።
ተቀማጭነቱን አሜሪካ ያደረገው "38 ኖርዝ ፕሮጀክት" የተባለ ተቋም በጥር ወር ባወጣው ሪፖርት ግን ሰሜን ኮሪያ በፈረንጆቹ 1990ዎቹ ካጋጠማት ረሃብ ወዲህ ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ቀውስ ትገኛለች ብሏል።